ሰንደቅ ዓላማ ኢትዮጵያውያን በአገር ሕልውና የሚቃጣ ጥቃትን ለመመከት የሚሰባሰቡት ኃይል ነው - ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
ሰንደቅ ዓላማ ኢትዮጵያውያን በአገር ሕልውና የሚቃጣ ጥቃትን ለመመከት የሚሰባሰቡት ኃይል ነው - ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ
አዲስ አበባ ጥቅምት 1/2014(ኢዜአ) ሰንደቅ ዓላማ ኢትዮጵያውያን በአገር ሕልውና የሚቃጣ ጥቃትን ለመመከት የሚሰባሰቡት ኃይል ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።
የአሁኑ ትውልድ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ክብር የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት ብለዋል።
14ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን "በአዲስ ምዕራፍ በተሟላ ሉዓላዊነት ለሰንደቅ ዓላማችን ከፍታ" በሚል መሪ ሃሳብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት ዛሬ ተከብሯል።
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዚህን ወቅት ሰንደቅ ዓላማችን በትውልዶች መስዋዕትነት ያስጠበቅ ነው የነጻነታችን ምልክት ነው ብለዋል፡፡
ሰንደቅ ዓላማ ለኢትዮጵያውያን የጋራ ማንነትና የጋራ መገለጫ እንዲሁም የአንድነት ተምሳሌት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ቀኑን ስናከብር ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ለሰንደቅ ዓላማ ዋጋ ከፍለው ነጻ አገር ያስረከቡንን አደራ በማስታወስ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪ ኢትዮጵያን በአዲስ ምዕራፍ ወደ ቀደመ ገናና ክብሯ እንድትመለስ ራዕይ የምንሰንቅበት ነው ብለዋል።
"ሰንደቅ ዓላማችን ኢትዮጵያውያን በአገር ላይ የሚሰነዘር የሕልውና ጥቃት ለመመከት የሚሰበሰቡት ኃይላቸው ነው፤የምናደረገው ትግል የሚሳካው በሰንደቅ ዓላማ ስር ባለው ኃይል ነው" ሲሉም ነው ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የገለጹት።
የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በሚመጥነው ክብርና ከፍታ ላይ ለማድረስ የተጀመሩ ሁሉን አቀፍ ለውጦችን ከዳር ማድረስ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ወጣቶች ለሰንደቅ ዓላማ የሚሰጠውን ክብር አስጠብቀው መቀጠል የሚችሉት ከእኛ በመማር መሆኑን መገንዘብ ይገባል ያሉት ፕሬዝዳንቷ፤ ከዚህ አኳያ የአሁኑ ትውልድ በሰንደቅ ዓላማ ስር ባለው ሃይል ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች በድል እንድታልፍ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት አመልክተዋል።
ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በሰንደቅ ዓላማው ያሉ የጋራ እሴቶችንና ማንነቶች ማስጠበቅ እንደሚገባው አሳስበዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የበዓሉ ተሳታፊዎችም ኢትዮጵያን ለዘመናት የሰንደቅ ዓላማቸውን ክብር ለማስጠበቅ መስዋዕትነት መክፈቻውንና አሁንም ይሄንን ክብር ለማስጠበቅ በአገር ፍቅር ስሜት መነሳታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን በሰንደቅ ዓላማው ስር በመሰባሰብና ከውስጥና ከውጭ የተቃጣባቸውን የሕልውና ጥቃት በመመከት በአገር ሉዓላዊነት እንደማይደራደሩ በተግባር እያሳዩ መሆኑን ተናግረዋል።
"እኛ ኢትዮጵያውያን የሰንደቅ ዓላማችንን ክብርና የሀገር ሉዓላዊነትን አናስደፍርም፤ ኢትዮጵያን ለመከፋፈል የቋመጡ ሃይሎችም ሕልማቸው አይሳካም" ብለዋል።
ሰንደቅ ዓላማ ያለውን ትርጉም ለሀገር ተረካቢ ትውልድ ማስተማር እንደሚገባም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።