አባይ ለኢትዮጵያ ከዘፈን ባለፈ በተግባር ሲሳይ ሊሆን መቃረቡን አረጋግጠናል - ኢዜአ አማርኛ
አባይ ለኢትዮጵያ ከዘፈን ባለፈ በተግባር ሲሳይ ሊሆን መቃረቡን አረጋግጠናል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1/2014 (ኢዜአ) የአባይ ወንዝ ለኢትዮጵያ ከዘፈን ባለፈ በተግባር ሲሳይ ሊሆን መቃረቡን አረጋግጠናል ሲሉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት አባላት ተናገሩ።
የምዕራባዊያንን ጫና ለመቀልበስና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለፍጻሜ እንዲበቃ ምክር ቤቱ ሚናውን ይቀጥላል ሲሉም አረጋግጠዋል።
ከተመሰረተ አንድ ዓመት የሞላው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት ልዑክ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ሰንቆ ወደ ምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ መምጣቱ የሚታወቅ ነው።
ልዑኩ ከያዛቸው ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጎብኝት በመሆኑ ከቱሪዝም ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ቦታውን ለመጎብኘት ትላንት ወደ ስፍራው አቅንቷል።
ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ እናት አገራቸው የመጡት የኢትዮጵያ የምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚ አባልና የልዑኩ አስተባባሪ አቶ አለባቸው ደሳለኝ፤ የጉብኝቱ ዋና ዓላማዎች ከሆኑት ተግባራት አንዱ በስፍራው ተገኝቶ በግድቡ ግንባታ ላይ የተሳተፉ ሰራተኞች ማመስገን ነው።
ከበርካታ ቢሮክራሲዎች በኋላ ኢትዮጵያን ወደ ክፍታ የሚወስደውን፤ በተለይም የኃይል ተጠቃሚ ላልሆኑ ዜጎች ተስፋ የሚሰጠውን የቃል ኪዳን ግድብ መመልከት ትልቅ ደስታ የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
በጉብኝታቸው የአባይ ወንዝ ለኢትዮጵያ ከዘፈን ባለፈ በተግባር ሲሳይ ሊሆን መቃረቡን ማረጋገጣቸውንም ተናግረዋል።
ከመላው ዓለም የተውጣጣ ዳያስፖራ ጉብኝቱን ማድረጉ ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጫና ለመቀልበስ ብሎም ለህዳሴ ግድብ ፍጻሜ መፋጠን ሚናውን ያጠናክር ዘንድ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል።
"ኢትዮጵያ አክብራናለች፤ እናከብራታለን" ብለዋል አቶ አለባቸው።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የዳያስፖራ አባላት የኢትዮጵያ ታላቁ ስጦታ የሆነውን ፕሮጀክት በማየታቸው ዕድለኛ እና ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ወደ መጡበት ሀገራት ሲመለሱ ለሌሎች የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ግንባታው ያለበትን ደረጃ የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰሩ ተናግረው፤ ሌሎች የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ግንባታውን በአካል ተገኝተው እንዲመለከቱ ጥሪ አቅርበዋል።
ግድቡ ተሽጧል የሚልና መሰል አሉባልታዎች ሲነዙብት እንደነበር አስታውሰው አሁንም ግንባታው በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ከ21 ዓመታት የውጭ አገር ቆይታ በኋላ ከሁለት ቀናት በፊት ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያን የመጡት የምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ አለማየሁ ስለሺ ግድቡ ተአምር ሆኖብኛል ይላሉ።
ከእንግሊዝ ለንደን ከ15 ዓመታት በኋላ የመጣው ጋዜጠኛ ዘውዱ መንግስቴም በተመሳሳይ ግድቡን በአካል በመጎብኝቱ መደሰቱና የወደፊት ተሳትፎውንም እንደሚያጠናክር ገልጿል።
ከ12 ዓመታት በኋላ ከአሜሪካ ሎሳንጂለስ የመጡት ጥንዶቹ አቶ ሚካኤል ጌታነህ እና ባለቤታቸው ወይዘሮ ሠርክአዲስ ዜና የግድቡ ግንባታ ከጠበቅነው በላይ የላቀ ሐሴት ፈጥሮብናል ብለዋል።
ከአሜሪካ ሎሳንጀለስ የመጡት አቶ ሙሉጌታ ምህረት ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያንን ሕይወት የሚለውጥና የሲሳይነቱን ፍሬ ለመቅመስ ጫፍ ላይ ያለን ፕሮጀክት በመጎብኝቴ ደስታዬ ወደር የለውም ብለዋል።
ዓለም አቀፍ ተቋማትና ምዕራባዊያን አገራት ማገዝ ሲገባቸው በኢትዮጵያ ላይ ጫና በማሳደር ግድቡ እንዲስተጓጎል እየሰሩ መሆኑን ገልፀው፤ ዓለም አቀፉ ጫና ኢትዮጵያዊያንን አንድ ያደረገ ዳግም አድዋ ስለመሆኑ አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ዳያስፖራው እያደረገ ያለው ሁለንተናዊ ተሳትፎ እየጎለበተ መምጣቱን ገልጸዋል።
''ኃያላን መንግስታት በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉት ያለው ጫና ዋናው መንስኤ በአባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው የህዳሴ ግድብ በመሆኑ በቁጭት በመነሳት ለፍጻሜው ሁለንተናዊ ድጋፍ ማድረግ ይገባል'' ብለዋል።
በመሆኑም ግድቡን በአካል ከመጎብኘት ባለፈ ዳያስፖራው በያለበት ለግድቡ በአምባሳደርነት እንዲሰራ፤ በገንዘብ ድጋፍና ቦንድ ግዥን ጨምሮም በዲፕሎማሲው መስክ ሚናውን እንዲወጣ ነው የጠየቁት።
ኢትዮጵያ 86 በመቶ የአባይ ምንጭ ብትሆንም የስሟ መጠሪያ ከመሆን ባለፈ ሳትጠቀምበት ዘመናት ነጉደዋል።
አባይ ኤሌክትሪክ እያመነጨልኝ ይፍሰስ በማለት ኢትዮጵያ ከ10 ዓመት በፊት የግድብ ግንባታ እውን ለማድረግ የመሰረት ድንጋይ ስታኖር ግብፆች “ምን ሲሆን” በማለት ኢትዮጵያን ሲያሻቸው በክስ ሲሞቃቸው ደግሞ በማስፈራራት ላይ ይገኛሉ።