የሰንደቅ ዓላማ ክብርን በመጠበቅ የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ጠላቶች መመከት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ተግባር ሊሆን ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሰንደቅ ዓላማ ክብርን በመጠበቅ የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ጠላቶች መመከት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ተግባር ሊሆን ይገባል
ጋምቤላ ፤ ጥቅምት 1/2014(ኢዜአ) የሰንደቅ ዓላማ ፍቅርና ክብርን በመጠበቅ የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ጠላቶች እኩይ ተግባር መመከት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ተመለከተ።
"በአዲስ ምዕራፍ በተሟላ ሉዓላዊነት ለሰንደቅ ዓላማችን" በሚል መሪ ሃሳብ ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ዛሬ በጋምቤላ ከተማ በድምቀት ተከብራል።
በበዓሉ አከባበር ሥነ-ሥርዓት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ እንዳሉት፤ ሰንደቅ ዓላማ የኢትዮጵያ ህዝቦች የህብር ብሄራዊ አንድነትና የሉዓላዊነት መገለጫ ዓርማ ነው።
የኢትዮጵያውያን ሉዓላዊነት ለማስከበር የተዋደቁላት ህያው ምልክት ከመሆኑም በላይ የድል አድራጊነት መግለጫም መሆኑን ገልጸዋል።
የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን የውስጥና ውጭ ታሪካዊ ጠላቶች በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ በማሳረፍ ደካማ ሀገር ለመፍጠር የጠነሰሱት ሴራ ከሽፎ ጠንካራ መንግስት በተገነባበት ማግስት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
በየዓመቱ የሚከበረው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በተለይም ወጣቱ ትውልድ ለብሄራዊ ሰንደቅ ዓላማ ያለውን ፍቅርና ክብር ለማጠናከር የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
የሰንደቅ ዓላማ ፍቅርና ክብር በመጠበቅ የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ጠላቶችን እኩይ ተግባር የመመከቱ ተግባር የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል።