ቀጥታ፡

''የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፊት አስቀድመን ሉዓላዊነቷንና የግዛት አንድነቷን ለማስከበር ሁሌም ዝግጁ ነን''

ጥቅምት 1/2014 (ኢዜአ)''የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፊት አስቀድመን ሉዓላዊነቷንና የግዛት አንድነቷን ለማስከበር ሁሌም ዝግጁ ነን'' ሲሉ የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ተናገሩ።

በመከላከያ ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤት የሚገኙ የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላትና አመራሮች የሰንደቅ ዓላማ ቀንን አክብረዋል።የመከላከያ ሚኒስቴር ሴቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ጥሩዬ አሰፌ፤ በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ሰንደቅ ዓላማውን ሰቅለዋል።በመርሃ ገብሩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሰራዊቱ አባላት ''ለኢትዮጵያ ሉአላዊነትና ለሰንደቋ ክብር ስንል ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ተዘጋጅተናል'' ብለዋል።

''የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፊት አስቀድመን ሉዓላዊነቷንና የግዛት አንድነቷን ለማስከበር ሁሌም ዝግጁ ነን'' ሲሉ አረጋግጠዋል።ከመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን ብርጋዴር ጀነራል አስፋው ማመጫ፤ የአገር ሉዓላዊነትና ክብር መገለጫ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ማክበር ሁላችንንም የሚያኮራ ነው ብለዋል።

''የሰራዊት አባል ስትሆን ደግሞ ሰንደቅ ዓላማ የተለየ ትርጉም አለው፣ ግዳጅህን ስትቀበል እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ነው'' ሲሉ ተናግረዋል።ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ ሁሉ ለብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ክብር ሲባል መሰዋዕትነት እየከፈሉ ማለፋቸውን አስታውሰው አሁንም ሰራዊቱ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመከፈል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የመከላከያ ሰራዊት ግንባታ ስራዎች ዕሕፈት ቤት አባል ኮለኔል ዘርይሁን ተሰማ፤ ''ሰንደቅ ዓላማ ሁሉንም ያስተሳሰረ የኢትዮጵያ ሉላዊነትና ግዛት አንድነት ማስከበሪያ መሆኑን ተናግረዋል።''ቀደምት አባቶቻችንም ይህንኑ ሲያደርጉ ማለፋቸውንና አሁንም ያለው ትውልድ ይህንን መንገድ እንደሚያስቀጥል አምናለሁ'' ብለዋል።

የመከላከያ የውጭ ግንኙነት አባል መቶ አለቃ መሰረት አበበ፤ ''አባቶቻችን ያወረሱን አገርና ሰንደቅ ዓላማ በክብር ለቀጣይ ትውልድ እናስረክባለን'' ብለዋል።በዚህም የአገር መከላከያ ሰራዊት ድርብ ሃላፊነት ስላለበት የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሰንደቅ አላማ ቀን በዓል የተከበረው ሰኔ 28 ቀን 2001 ዓ.ም መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም