ቀጥታ፡

አዲስ ተሿሚዎች ከሌብነትና ብልሹ አሰራር በፀዳ መልኩ ህዝብን ልታገለግሉ ይገባል

አዲስ አበባ ጥቅምት1/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ለማገልገል እድል የተሰጣቸው አዲስ ተሿሚዎች ከሌብነት እና ብልሹ አሰራር በፀዳ መልኩ ህዝብ ሊያገለግሉ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሳሰቡ።

ለከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ስልጠና መሰጠት ተጀምሯል።

በስልጠናው ማስጀመሪያ ላይ መልእክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዝብ እና ታላቋን ኢትዮጵያ ለማገልገል እድል የተሰጣችሁ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።

አዲስ ተሿሚዎች ህዝብን በቅንነት ለማገልገልና ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና ለማሸጋገር ታላቅ አደራ ተጥሎባችኋል በማለት የኢትዮጵያን ህዝብ ከሌብነት እና ብልሹ አሰራር በፀዳ መልኩ ማገልገል አለባችሁ ሲሉ አሳስበዋል።

የተሰጠንን ሃላፊነት አገር የምናገለግልበት መሣሪያ በማድረግ ህዝባችንን በቀናነትና በታማኝነት ልናገለግለው ይገባል" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ኢትዮጵያን ለመቀየር ከዚህ ቀደም ያልታዩ ጉዳዮችን በመዳሰስ ለብልፅግና መትጋት አለባችሁ ሲሉም ተናግረዋል።

የአሁኑ ስልጠና በዋነኛነት ዓላማው ማሳወቅ፣ ማነሣሣት እና ለቡድን ስራ መዘጋጀት መሆኑንም ጠቁመዋል።

ለአምስት ተከታታይ ቀናት በሚሰጠው ስልጠና ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች እንዲሁም የሁለቱ ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች ተገኝዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም