ቀጥታ፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራምና ዩኒሴፍ ኃላፊዎች የሶማሌ ከልል ተፈናቃዮችን ጎበኙ

አዲስ አበባ ነሀሴ 11/2010 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የዓለም ምግብ ፕሮግራምና የህፃናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) ዳይሬክተሮች የሶማሌ ክልል ተፈናቃዮችን ጎበኙ። በኢትዮጵያ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተር ስቴቨን ኦማሞ እና የዩኒሴፍ ተወካይ ጊሊያን ሜልሶፕ በግጭቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎችየሚደረገውን ድጋፍ ጎብኝተዋል። ስቴቨን ኦማሞ እንዳሉት፤ ተፈናቃዮቹ ለበርካታ ችግሮች የተጋለጡ በመሆኑ ከደረሰባቸው ችግሮች ለማውጣት አስፈላጊው ዕርዳታ እየተደረገላቸው ነው። በኢትዮጵያ መንግስትና በግብረ ሰናይ ድርጅቶች በኩል እየተደረገ ያለውን የሰብዓዊ ዕርዳታ አድንቀዋል። በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ጊሊያን ሜልሶፕ በበኩላቸው ሴቶችና ህፃናት የውኃና የጤና አገልግሎት ችግር የተጋለጡ በመሆኑ ተቋርጠው የነበሩ የዕርዳታ ፕሮግራሞችን በማስጀመር ከመንግስትና ከሌሎች ተባባሪ አካላት ጋር በመሆን እንደሚሰሩ አስታውቀዋል። ድርጅቱ ለሴቶችና ህፃናት የብስኩት፣ የውኃ ማከሚያ ኬሚካል፣ ሳሙናና ብርድ ልብስ እያቀረበ ሲሆን በዓለም ምግብ ፕሮግራም በኩል የሩዝ፣ የዘይትና፣ የጥራጥሬዎችና የበቆሎ ምግቦች እያቀረበ መሆኑን ድርጅቱ በመግለጫው አመልክቷል። የኢትዮጵያ መንግሥት ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሰብዓዊ ዕርዳታ ኮሚቴ አቋቁሞ ለተፈናቃዮች የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የተፈናቃዮች ቁጥር 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም