ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የተለያዩ ፈተናዎችን ተቋቁማ ጸንታ የቀጠለችው ኢትዮጵያውያን ለሰላም ባላቸው ጽኑ ፍላጎት ነው

መስከረም 30 / 2014 (ኢዜአ) "ኢትዮጵያ የተለያዩ ፈተናዎችን ተቋቁማ ጸንታ የቀጠለችው ኢትዮጵያውያን ለሰላም ባላቸው ጽኑ ፍላጎት ነው" ሲሉ የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዱዓለም ተናገሩ፡፡

የሰላም ሚኒስቴር ስራቸውን የተረከቡትና ከሚኒስቴሩ አመራሮች ጋር ትውውቅ ያደረጉት አቶ ብናልፍ የተጀመሩ መልካም ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ችግር መልክ ብዙ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ '' ሕዝቡ ከአዲሱ መንግስት ብዙ ይጠብቃል'' ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶች በዜጎች ላይ ሞትና መፈናቀል ማስከተላቸውን አስታውሰው፤ "ኢትዮጵያውያን በሰላም ወጥተው እንዲገቡ በትኩረት ይሰራል" ብለዋል፡፡

May be an image of 1 person, standing, headscarf, flower and indoor

ለዚህ ደግሞ የህግ የበላይነት መከበር ዋነኛው ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም ወዳድነቱን በተግባር እንደሚያሳይ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የሰላም ዋጋ ከፍ ያለ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ የተለያዩ ፈተናዎችን ተቋቁማ ጸንታ የቀጠለችው ኢትዮጵያውያን ለሰላም ባላቸው ጽኑ ፍላጎት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"የተለያየ የፖለቲካ ፍላጐት ያላቸው ሀይሎች በሚፈጥሩትን ችግር ሁሉ ተቋቁማ አገሪቷ አሁንም ጠንካራ ሆና መቀጠል የቻለችው በሕዝቡ የሰላም ፍላጎት ነው" ብለዋል።

"ሕዝቡ ይህን የሰላም ፍላጎት አጠናክሮ መቀጠል አለበት'' ያሉት የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ፤ ሰላም ሁሉንም ማሸነፍ የሚችል ትልቅ ሃይል መሆኑን አስገንዝበዋል።

ዜጎች ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት በኢትዮጵያ ህልውና ላይ ግልጽ አደጋ የደቀኑ ኃይሎችን መመከት እንዳለባቸውም አሳስበው፤ የጸጥታ ሀይሉና ሕዝቡ ያላቸው ቅንጅት ይበልጥ እንዲጎለብት በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም