ኦቢኤን ለተጎዱት ድምጽ ከመሆን ባለፈ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ አጋርነቱን ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ኦቢኤን ለተጎዱት ድምጽ ከመሆን ባለፈ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ አጋርነቱን ይቀጥላል
ደሴ መስከረም 30/2014 (ኢዜአ ) ኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦቢኤን) ለተጎዱ ወገኖች ድምጽ ከመሆን ባለፈ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ አጋርነቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዝናቡ አስራት ገለጹ።
ኦቢኤን፣ በላይና ተስፋ መኪና መሸጫና ፌድራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ በውርጌሳ ለተጠለሉ ተፈናቃዮች 8 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብ እህልና ቁሳቁስ ዛሬ ድጋፍ አድርገዋል።
ስራ አስኪያጁ በድጋፍ ርክክቡ እንዳሉት አሸባሪው የህውሃት አሸባሪ ቡድን የኢትዮጵያን ህዝብ ከፋፍሎ አገር ለማፍረስ የሸረበውን ሴራ ለማክሸፍ ሁሉም መረባረብ አለበት።
ውስጣዊ አንድነታችንን ጠብቀን ኢትዮጵያን ከገጠማት አሁናዊ ውስብስብ ችግር ለማላቀቅ የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ ተናግረዋል።
“ለተበደለው ህዝብ ድምፅ ከመሆን ባለፈም ለተፈናቃዮች የምንችለውን ድጋፍ በማድረግ የድርሻችንን እየተወጣን ነው” ብለዋል።
“ዛሬም ሰሜን ወሎ ተገኝተን በውርጌሳ ከተማ ለተጠለሉ ተፈናቃዮች 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት 500 ኩንታል ዱቄትና ሩዝን ጨምሮ የተለያዩ አልባሳት ድጋፍ አድርገናል” ብለዋል።
ሁሉም የሚችለውን ማድረግ አለበት ያሉት ስራ አስኪያጁ ኦቢኤን በዚህ ዓመት ብቻ ለተለያዩ ማህበረሰብ አገልግሎቶች ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ አድርጓል ፤ይሔም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ሌላው ድጋፍ አድራጊ የበላይና ተስፈ መኪና መሸጫ ባለቤት አቶ በላይነህ ደበበ በበኩላቸው 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚገመት 300 ኩንታል ዱቄት ለተፈናቃዮች ፣ 30 ሰንጋ ለመከላከያና ለፀጥታ አባላት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል ።
“አገር ከሌለ መኖር ስለማይቻል የምንችለውን ደግፈን ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ እናደርጋለን ፣ድጋፈየም ይቀጥላል” ብለዋል።
ወቅቱ ተጋግዘን አገርን የምናሻግርበት ነው ያሉት የፌዴራል ህብረት ስራ ኮምሽን ተወካይ አቶ ዳሬቦ ቡሴር ናቸው ።
2 ነጥብ 5 ሚለውን ብር የሚገመት ቁሳቁስና አልባሳት ድጋፍ ከማድረጋቸውም ባለፈ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት በቅንጅት በመስራት ሃላፊነታችንን እንወጣለን ብለዋል አቶ ዳሬቦ።
ድጋፉን የተረከቡት የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ወልደትንሳኤ መኮንን በበኩላቸው በአሸባሪው ተፈንቅለው ውርጌሳ ከተማ የተጠለሉ ተፈናቃዮች ቁጥር ከ30 ሺህ ማለፉን ገልጸዋል።
“ዛሬ ተቋማት በቦታው ተገኝተው ያደረጉት ድጋፍ ቀጠናው ሰላም መሆኑን በተግባር ከማረጋገጡም ባለፈ ችግሩን ስለሚያቃልል እናመሰግናለን” ብለዋል።
ከተፈናቃዮች መካከል ወይዘሮ ጉሪሴ ሲሳይ በሰጡት አስተያየት የ4 ልጆችን እናት የሆነች ልጃቸው ከአንድ ልጇ ጋር በግፍ ተገድላለች” ብለዋል።
ሶስት የሙት ልጆችን ይዘው ለርሃብ መጋለጣቸውን ጠቁመው “ድጋፉ ችግራችንን ያቃልለዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
“የኢትዮጵያ ህዝብ ከሚያደርገው ድጋፍ ባለፈ ቡድኑን እንዳይነሳ አድርጎ በመቅበር ሊክሰን ይገባል” ብለዋል።
በድጋፉ ላይ የሰሜን ወሎ ዞን፣የሀብሩ ወረዳ አመራሮች፣ ባለድርሻ አካላትና የተፈናቃዮች ተወካዮች ተገኝተዋል ።