የቴክኖሎጂ ከተማ በባህር ዳር ከተማ ሊገነባ ነው

99
ባህር ዳር ነሀሴ 11/2010 ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ከተማ በባህር ዳር ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን የአማራ ክልል ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ኮሚሽን አስታወቀ። የቴክኖሎጂ ከተማው ግንባታ የሚካሄደው በጢስ አባይ ሳተላይት ከተማ እንዲሆን የቦታ መረጣ ተደርጓል። የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር ሰብስበው አጥቃው ዛሬ ለኢዜአ እንዳሉት የቴክኖሎጂ ከተማው ግንባታ የሚካሄደውም ከአሜሪካ በመጡ የፊልም ባለሙያዎችና ባለሃብቶች ነው፡፡ የቴክኖሎጂ ከተማው ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ በዘርፉ አለም የደረሰበትን በቀላሉ ለማምጣትና  የእውቀት ሽግግር ለማድረግ የጎላ ሚና ይጫወታል፡፡ " በውስጡም  በቴክኖሎጂ የበለፁጉ ማዕከላት ይኖሩታል "ያሉት ኮሚሽነሩ የቴክኖሎጂ ምርምርና የፈጠራ ማዕከላት እንደሚኖሩትም  ጠቁመዋል፡፡ የቴክኖሎጂ ገበያ ትስስርና ሌሎችም ማዕከላት ለሚኖሩት ለቴክኖሎጂ ከተማው ግንባታ የሚያስፈልገው ወጪ ከ145 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነም  አመልክተዋል። ለቴክኖሎጂ ከተማው ግንባታ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንዲሁም የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ኮሚሽን  ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ዶክተር ሰብስበው አስታውቀዋል። ፐሮጀክቱ ወደ አካባቢው እንዲመጣ የክልሉ አመራሮችና የዳያስፖራ አባላት ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውንም  ጨምረው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም