የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝበ ውሳኔ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ክልል እንሁን የሚል ድምጽ አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝበ ውሳኔ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ክልል እንሁን የሚል ድምጽ አገኘ
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝበ ውሳኔ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ክልል እንሁን የሚል ድምጽ ማግኘቱን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ የምርጫ ውጤቱን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
ሕዝብ ውሳኔው ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ኮንታ ልዩ ወረዳ፣ ምዕራብ ኦሞ ዞን፣ ቤንች ሸኮ ዞን፣ ከፋ ዞን፣ ዳውሮ ዞንና ሸካ ዞንን ያካተተ ነው።
በመግለጫቸውም መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ አብዛኛው ድምጽ ሰጪ ክልልነትን መርጧል ብለዋል።
ለድምጽ አሰጣጡ ከተመዘገቡት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን መራጮች ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የሚሆን መራጮች ክልል እንሁን የሚል ድምፅ መስጠታቸውን ገልጸዋል።
ይህም ከጠቅላላ ድምፅ ሰጭዎች 93 ነጥብ 9 በመቶ ምርጫቸው ክልል መሆን ሆኗል።
በህዝበ ውሳኔው 24 ሺህ መራጮች ደግሞ በደቡብ ክልል ስር መቆየትን መርጠው ድምፅ መስጠታቸውን ገልጸዋል።
ለሕዝበ ውሳኔው 22 የምርጫ ክልሎች የተደራጁ ሲሆን 1 ሺህ 613 የምርጫ ጣቢያዎችም ተዘጋጅትው ነበር።
ከዚህ ባለፈም 1 ሺህ 424 የሲቪል ማሕበራት ተወካዮች የሕዝበ ውሳኔውን ሂደት መታዘባቸውን አቶ ውብሸት ገልጸዋል።
የተገኘውን የህዝበ ውሳኔ ውጤት ቦርዱ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ያቀርባል ብለዋል።