አንድነት ፓርክን ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ590 ሺህ በላይ ቱሪስቶች ጎብኝተውታል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29/2014(ኢዜአ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እውን የሆነውን አንድነት ፓርክ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ590 ሺህ በላይ ቱሪስቶች ጎብኝተውታል።

ፓርኩ የተመሰረተበትን ሁለተኛ ዓመት በዛሬው ዕለት በማክበር ላይ ሲሆን የአንድነት ፓርክ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታምራት ሃይሌ፤ የፓርኩን የሁለት ዓመት ጉዞ በማስመልከት ማብራሪያ ሰጥተዋል። 

የፓርኩን እውን መሆን ሃሳቡን ላመነጩት እና ላቋቋሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ምስጋና ይገባል ብለዋል።

ፓርኩን በሁለት ዓመት ጉዞው ከ590 ሺህ በላይ ቱሪስቶች የጎበኙት መሆኑን ገልጸው ከጎብኚዎቹ መካከልም 487 ሺህ የሚሆኑት በክፍያ የገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከ100 ሺህ የሚልቁት ደግሞ ያለክፍያ በነፃ ጉብኝት መግባታቸውን ገልጸዋል።


ፓርኩን ከ25 ሺህ በላይ የውጪ ዜጎች መጎብኘታቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ በአሁኑ ጊዜ የአገርን ገጽታ ከመገንባት አንጻር የጎላ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።

የአንድነት ፓርክ እውን መሆን የአይቻልም መንፈስ የተሰበረበት ነው ያሉት ዋና ዳይይክተሩ የአገርን ገጽታ ከማስተዋወቅ አንጻር ሰፊ ስራ መሰራቱንም ተናግረዋል፡፡

ፓርኩ መንግስት ቃል በተግባር ለመተርጎሙ ታላቅ ማሳያ ነው ያሉት ዶክተር ታምራት፤ ጎብኚዎችም የቁስና የአዕምሮ ብልጽግናን ያገኙበት ስፍራ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡ 

ፓርኩ የአገርን ገጽታ በመገንባት ሂደት በአዲስ ምዕራፍ መዘጋጀቱን አመልክተው ሰራተኞቹም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት በብቃት ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የአንድነት ፓርክ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩንም ተናግረዋል።

የአንድነት ፓርክ በኮቪድ-19 ምክንያት ለ6 ወራት ተዘግቶ እንደነበር የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም