ከጥንት እስከ ዛሬ ስራ ላይ የዋሉ ቴምብሮች ለእይታ ቀረቡ - ኢዜአ አማርኛ
ከጥንት እስከ ዛሬ ስራ ላይ የዋሉ ቴምብሮች ለእይታ ቀረቡ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 29/2014 ( ኢዜአ በኢትዮጵያ ከጥንት አስከ ዛሬ ሲያገለግሉ የነበሩ ቴምብሮች ለእይታ ቀረቡ።
የዓለም ፖስታ ህብረት የተመሰረተበት 147ኛ ዓመት "በፈጠራ ማገገም (Innovate to Recover)" በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።
ይህንን ተከትሎ በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የተዘጋጀው የቴምብር አውደ ርእይ ከዛሬ ጀምሮ ለሰባት ተከታታይ ቀናት ለህዝብ ክፍት ይሆናል።
የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሃና አርአያስላሴ፤ እንደተናገሩት ድርጅቱ ከ1886 ዓ.ም ጀምሮ የፖስታ አገልግሎትን ጨምሮ የተለያዩ የህዝብ አገልግሎቶችን ሲሰጥ የቆየ አንጋፋ ተቋም ነው።
በዚህ ሂደት የተለያዩ ቴምበሮች አገልግሎት ላይ መዋላቸውን ገልጸው ከጥንት እስከ ዛሬ አገልግሎት ላይ የዋሉ ታሪካዊ ቴምብሮች ከዛሬ ጀምሮ ለህዝብ ለእይታ ክፍት መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከ1901 ዓ.ም ጀምሮ የአለም ፖስታ ህብረት አባል ሆና መዝለቋን ጠቁመው የፖስታ አገልግሎት በተለያዩ ፈተናዎች እያለፈ አሁን ላይ ደርሷል ብለዋል።
ለዚህም መላው የፖስታ አገልግሎት ድርጅት ሰራተኞች ጥረት የማይተካ ሚና እንዳለው ወይዘሮ ሃና ተናግረዋል፡፡
በዛሬው እለት የአውደ ርእዩን መከፈት ተከትሎ በርካታ ሰዎች ታድመው ታሪካዊዮቹን ቴምብሮች ተመልክተዋል።
ከታዳሚዎቹ መካከል መምህርና ደራሲ ታደሰ ስዩም ታሪክ እያሸጋገረ አምጥቷቸው ተሰንደው ዛሬ ላይ ለእይታ በበቁት ቴምብሮች መደሰታቸውን ተናግረዋል።
በቴምብሮች ታሪክን፤ ባህል እና ማንነታቸውን ሰንዶ ማቆየትና ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚቻል ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል።
መምህርና ሰአሊ ዘራዳዊት አባተ፤ ቴምብሮች የአንድን አገር ባህል፣ ወግ፣ ማንነትና የታሪክ ሂደት በቀላሉ የሚገልጹና የሚያሳዩ መሆኑን አብራርተዋል።
ከጥንት አስከ ዛሬ አገልግሎት ላይ የዋሉ ቴምብሮችን ለህዝብ ማሳየትም ትልቅ መልእክት አለው ብለዋል።
የዓለም ፖስታ ህብረት የተመሰረተበት 147ኛ ዓመት ዘንድሮ በ192 አባል አገራት በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።