ቀጥታ፡

የመሪዎቹ መልዕክት የፓን አፍሪካኒዝምን እሳቤ የሚያጠናክር ነው

ሚዛን አማን፤ መስከረም 29/2014( ኢዜአ) በጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓለ ሲመት ላይ የተገኙ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች መልዕክት የፓን አፍሪካኒዝምን እሳቤ የሚያጠናክር መሆኑን የታሪክ ምሁራን ተናገሩ።

የመሪዎቹ ንግግር ኢትዮጵያን ለማግለል ለሚሹ ምዕራባውያን የአፍሪካ ሀገራት ራሳቸውን ከኢትዮጵያ ለይተው እንደማያዩና የአንድነት መሰረት ላይ መቆማቸውን ያመላከተ መሆኑን ምሁራኑ ለኢዜአ ገልጸዋል።


የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁር ታማኝ ወይሳ  በሰጡት አስተያየት፤ መሪዎቹ የኢትዮጵያን ትንሣኤ ከታሪክ ጋር እያስተሳሰሩ መግለጻቸውን አስታውሰዋል።


ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት ምስረታ ያላትን ሚና እንዲሁም በሰላም ማስፈን ሥራዎች ላይ ያበረከተችው አስተዋጽኦ ገናናነቷን የሚያሳይ ሆኖ በመሪዎቹ መጠቀሱ ፓን አፍሪካኒዝምን ለማጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል።


መሪዎቹ ኢትዮጵያ በራሷ ችግር ውስጥ ሆና ለችግራቸው የምትደርስ ሀገር በመሆኗ ''ኢትዮጵያ የአፍሪካ እናት ነች'' ማለታቸውን በማሳያነት አንስተዋል።


የኢትዮጵያ ህመም የሌሎች አፍሪካ ሀገራት ህመም መሆኑን መሪዎች በመልዕክታቸው ማንሳታቸውን የገለጹት ምሁሩ "ይህ አቋማቸውና ያንጸባረቁት ሀሳብ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ለመነጠል የሚሹ አካላትን አንገት የሚያስደፋና ምኞታቸውን ከንቱ የሚያደርግ ነው" ብለዋል።


"ደማቁን ታሪካችንን ለማስቀጠል አንድነታችንን እንደ ትላንቱ አጠናክረን መሄድ ይጠበቅብናል" ያሉት ደግሞ በዩኒቨርስቲው በማህበረሰብ ሳይንስ ትምህርት ኮሌጅ የታሪክ ትምህርት ክፍል ኃላፊ  አጥናፉ ምትኩ ናቸው።


''የአድዋ ነጸብራቅ ዛሬም በኢትዮጵያ እየበራ ነው፤  አንድነታችንና ነጻነታችን በኢትዮጵያ ብቻ ተገደቦ የሚቀር ሳይሆን ለአፍሪካም ትሩፋት ነው ሲሉ አክለዋል።


ለዚህም የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በበዓለ ሲመቱ ቀን ያደረጉት ንግግር ህያው ምስክርና ለኢትዮጵያዊያን  የሞራል ስንቅ መሆኑን ጠቅሰዋል።


የኢትዮጵያን ታሪክና እውነት በቅጡ ያልተረዱት ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ይህን እንዲገነዘቡና የቀድሞ ክብራችንና ልዕልናችን ተጠናክሮ እንዲቀጥል የዲፕሎማሲ ሥራ ሊጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።


በዚህ ረገድ አዲሱ መንግስት ትልቅ የቤት ሥራ እንደሚጠበቅበት አመላክተዋል።

በበዓለ ሲመቱ ላይ የተገኙት የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በመልዕክታቸው ኢትዮጵያን እናታችን ማለታቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም