አዲሱ ትውልድ ፈተናዎችን አሸንፎ በማለፍ ለኢትዮጵያ እድገትና ለውጥ ለማምጣት መስራት ይኖርበታል - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ ትውልድ ፈተናዎችን አሸንፎ በማለፍ ለኢትዮጵያ እድገትና ለውጥ ለማምጣት መስራት ይኖርበታል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 29/2014 (ኢዜአ) አዲሱ ትውልድ ወቅታዊ ችግሮችን አሸንፎ በመሻገር ለኢትዮጵያ እድገትና ለውጥ የሚያመጣ መሆን ይኖርበታል ሲሉ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።
ፕሬዚዳንቷ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ በክብር እንግድነት በመገኘት ለተመራቂዎችና ቤተሰቦቻቸው የእንኳን ደስ ያላችሁ መልአክት አስተላልፈዋል።
የተመራቂዎቹ ደስታ ከቤተሰብና ከወዳጆቻቸው ባለፈ በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ እያለፈች ያለችው ኢትዮጵያ ጭምር ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የጀመረችውን ለውጥ ውጤታማ ለማድረግ በዕውቀትና ክህሎት የዳበረ የሰው ኃይል ያስፈልጋል፣ የዛሬ ተመራቂዎች ደግሞ ለዚህ ስኬት ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ።
የኮቪድ 19 ወቅታዊ ፈተናን በመቋቋም እና የአሸባሪዎችን ኢትዮጵያን የማፍረስ እቅድ ለማክሸፍ እየሰራን የተለያዩ ስኬቶችን ማስመዝገብ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህ ውስብስብና አስቸጋሪ ወቅት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመማርና ማስተማር ስራውን በብቃት በመወጣት ተማሪዎቹን ለምረቃ ማብቃቱን አድንቀዋል።
ዩኒቨርስቲው በጥናትና ምርምር አቅሙን ከፍ ለማድረግና ለማሻሻል እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው የትምህርት ጥራት በማረጋገጥ ረገድ ይበልጥ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።
"ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኢትዮጵያ ብዙ ትጠብቃለች" ያሉት ፕሬዝዳንት ሳሕለወርቅ፤ ዩኒቨርሲቲው ካስቀመጠው ግብ አኳያ ለስኬት ብዙ መጣር ይጠበቅበታል ነው ያሉት።
ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ አገልግሎት በርካታ ተግባራትን መከወን አለበት፣ ተመራቂዎች የስራ ክህሎት ስልጠናም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።
እንደ አገር ካጋጠሙን ፈተናዎች ለመውጣት በሚደረገው ትግል የዛሬ ተመራቂዎች የድርሻቸውን በመወጣት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
አዲሱ ትውልድ ወቅታዊ ችግሮችን አሸንፎ በመሻገር ለኢትዮጵያ እድገትና ለውጥ የሚያመጣ መሆን ይኖርበታል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች የተጎዱትን መደገፍ፣ የወደመውን መገንባት፣ ሰላምንና ልማትን ማጠናከር የወጣቶች ትልቅ ሃላፊነት ሊሆን ይገባዋል ብለዋል ፕሬዝዳንቷ።
በአገር ጉዳይ ቁሞ መመልከት ሳይሆን ተስፋና መፍትሔ ሆኖ በተግባር መገኘት ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል።