ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከተመድና የሰብአዊ ድጋፍ ተልዕኮን ብቻ ከሚያከናውኑ ተቋማት ጋር በቅርበት ለመስራት ዝግጁ ናት

መስከረም 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የሰብአዊ ድጋፍ ተልዕኮን ብቻ ከሚያከናውኑ አለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅርበት ለመስራት ዝግጁ መሆኗን በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዘነበ ከበደ ገለጹ።

ከተሰጣቸው ተልዕኮ ውጪ ሲንቀሳቀሱ የተገኙ የተመድ ሰራተኞች ከሀገር እንዲወጡ መደረጋቸውን በተመለከተና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዘነበ ከበደ ከአር ኤስ አይ ራዲዮና ቴሌቪዥን ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አምባሳደሩ በዚህ ወቅት የሰብአዊ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት ወደ ኢትዮጵያ በሚመጡበት ጊዜ አለም አቀፍ ደንቦችንና የሀገሪቱን ህግ ባከበረ መልኩ ለመንቀሳቀስ ስምምነት ማካሄዳቸውን ተናግረዋል።

ይህም በሁለትዮሽ የጋራ ጥቅምን ባስከበረ ስምምነት ለረጅም ዘመናት ሲሰራበት የቆየ መሆኑን ገልጸዋል።

ከቀናት በፊት ደግሞ ከተሰጣቸው ተልዕኮና ከሰብአዊ ተቋማት አላማ ውጪ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሰባት ግለሰቦች ከኢትዮጵያ መባረራቸውን አስታውሰው፤ ጉዳዮ ከተመድ ወይንም ከሌሎች ሰብአዊ ድርጅቶች ጋር የተፈጠረ ችግር አለመሆኑን አመልክተዋል።

መንግስት ከአገር ያስወጣቸው ግለሰቦች ከተሰጣቸው ተልዕኮ ውጪ የተንቀሳቀሱና ከአሸባሪ ድርጅት ጋር ሲሰሩ የነበሩ ናቸው ብለዋል።

ግለሰቦቹ በአንድ አገር ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ ሲገቡ የነበሩና ከዚህ ድርጊታቸው ሊታቀቡ ያልቻሉ መሆናቸውን አስታውቀው የግለሰቦቹን ድርጊት መንግስት በተደጋጋሚ ጊዜ ለተመድ ቢያስታውቅም ድርጅቱ ምላሽ አለመስጠቱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳይዋ ጣልቃ የሚገቡ ግለሰቦችን ያለማንም ፈቃድና ለማንም ሳታሳውቅ ከአገር የማስወጣት እንደምትችልም መናገራቸውን አር ኤስ አይ ኒውስ ዘግቧል።

በአሁኑ ወቅትም ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር የኢትዮጵያ መንግስት በቅርበት ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ገልጸው ከአገር በተባረሩት ምትክ የሰብአዊ ድጋፍ ተልእኳቸውን ብቻ ለመወጣት የሚመጡ ሰራተኞችን ለመቀበል ኢትዮጵያ ዝግጁ ናት ሲሉም አስታውቀዋል።

“በተሰጣቸው ተልዕኮ መሰረት ከሚንቀሳቀሱ ከሌሎች አለም አቀፍ ሰብአዊ ድርጅቶችና ተቋማት ጋር በአለም አቀፍ ህጎች መሰረትና የሁለትዮሽ ጥቅምን ባከበረ መልኩ ለመስራትም ዝግጁ ነን” ሲሉ ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም