ሰብአዊነትን ሽፋን ያደረገ የሴረኞች ደባ - ኢዜአ አማርኛ
ሰብአዊነትን ሽፋን ያደረገ የሴረኞች ደባ
ሰባት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰራተኞች የተመደቡበትን ሰብዓዊ አገልግሎት በገለልተኛነት፣ በሰብዓዊነትና በነጻነት መሥራት ሲገባቸው ሀሰተኛና የተዛባ መረጃ በማስተላለፍ፣ የጦር መሣሪያ በማቀበልና በሌሎች የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በመሳተፍ ለአሸባሪው የህወሓት ቡድን ሲሰሩ በመገኘታቸው መንግስት በ72 ሰዓት ውስጥ ሀገር ለቀው እንዲወጡ አድርጓል። ከአገር እንዲወጡ የተወሰነባቸው ግለሰቦች ሙያዊ ሥነ ምግባራቸውንና የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ አገልግሎት መርህን በመጣስ የአሸባሪውን ቡድን ሴራ ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ ተገኝተዋል።
ከመንግስት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እነዚህ የተመድ ሠራተኞች በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት ምክንያት በርካታ ንፁሃን ሰዎች መገደላቸውን በተጋነነ ቁጥር በመግለጽ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መሬት ላይ የሌለን መረጃ ሲያሰራጩ ነበር። በረሃብ ያልሞቱ ሰዎችን እንደሞቱ በመቁጠር የተረጂዎችን ቁጥር በሚሊየን በመጨመርና በሌሎችም ጉዳዮች ለቡድኑ ያላቸውን ወገንተኝነት በሚያረጋግጡ ተግባራት ተሳትፈዋል። ሠራተኞቹ የሰብዓዊ አገልግሎታቸውን ወደ ጎን ትተው የተሟጋችነት ሚና እንደነበራቸውና ለአሸባሪው ቡድን የምግብ፣ የመድሃኒት፣ የመገናኛ አገልግሎት እና የመሳሰሉትን እርዳታዎች ሲያደርጉለት እንደቆዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ኢትዮጵያ በሉአላዊ መብቷ ተጠቅማ ድርጅቶቹ ሀገር ለቀው እንዲወጡ የወሰደችው እርምጃ በዓለም የመጀመሪያው እስኪመስል ድረስ የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አንገብግቦታል። በዚህም ጉዳዬ ብሎ ኢትዮጵያ ላይ ለማሴር ስብሰባ ተቀምጧል። የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በአሸባሪው ህወሓት ስለተያዙት የእርዳታ ማመላለሻ መኪኖች ከማስረዳት ይልቅ መንግስት እርዳታ እንዳስተጓጎለ ለማስረዳት ጥረት አድርጓል። ዋና ጸሐፊው በአሜሪካ እና እንግሊዝ ከሚደገፉት እንዲሁም በአየርላንድ ከሚመከሩት የጁንታው አክቲቪስቶች እና ሎቢስቶች የተቀበለውን ወሬ ቁምነገር አድርጎ አቅርቧል። በህዝብ ድምጽ ለተመረጠው መንግስት እውቅና ሳይሰጡ “መንግስት መረጃ ሳይሰጠን እርምጃ ወስዷል” በሚል ከሰዋል።
አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ከዚህ ቀደም በተለያዩ አገራት የነበሩ የተመድ ሠራተኞች እንደተባረሩ አስታውሰው፣ ሆኖም የፀጥታው ምክር ቤት አንድም ጊዜ ተወያይቶበት እንደማያውቅ አንስተዋል።
አሜሪካ ከሁለት ዓመታት በፊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ሊደረግ ጥቂት ቀናት ሲቀረው የኩባ ዜግነት ያላቸው ሁለት የተ.መ.ድ ሰራተኞች በአስቸኳይ ሀገሪቱም ለቀው እንዲወጡ አድርጋለች። የትራምፕ አስተዳደር ለማባረሩ በምክንያትነት ያቀረበው ኩባውያን የተመድ ሰራተኞች አሜሪካን እየሰለሉ ነው የሚል ነበር።
የቀረበው ምክንያት አሳማኝ እንዳልሆነ አሜሪካ ለቀረበላት ጥያቄ “ሰራተኞቹ አሜሪካ ውስጥ መገኘታቸው ራሱ ለብሄራዊ ደህንነት ስጋት የሚፈጥር በመሆኑ ለቀው እንዲወጡ ተደርጓል” ነበር ያለችው። አሜሪካ በዚህም አለበቃች። ለአገሪቷ ጥቅሞች ስጋት ይፈጥራሉ ባለቻቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ ምርመራ በማድረግ ማባረሯን እንደምትቀጥል እቅጩን ተናግራለች።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሲመሰረት መቀመጫውን ኒውዮርክ ከተማ እንዲሆን ወስኗል። ድርጅቱ መቀመጫውን ኒውዮርክ ሲያደርግ ግን አሜሪካ የተ.መ.ድ ሰራተኞችን ከአገር የማስወጣት ሂደት ላይ መከተል የሚገባትን አካሄድ እ.ኤ.አ በ1947 የመንግሥታቱ ድርጅት መቀመጫ ስምምነትን (U.N. Headquarters Agreement) ላይ በግልጽ አስፍሯል። በዚህም አሜሪካ የድርጅቱን ሰራተኞች ተቀብላ የማስተናገድ ሞራላዊ ግዴታ አለባት። ሃቁ ይህ ሆኖ ሳለ አሜሪካ በኩባውያን ሰራተኞች ላይ የፈጸመችው ተግባር ከዚህ የተቃረነ ነው። ባስ ሲልም ተልዕኳቸውን ‘አላመንኩበትም’ የምትላቸውን ተቀጣሪዎች የደህንነት ስጋት አሊያም ከውጭ ግንኙነት ፖሊሲዎች ጋር በማያያዝ የመግቢያ ቪዛ እንደምትከለክል እወቁት ብላም ነበር።
አሜሪካ እነዚህንና መሰል ተግባራት በመንግሥታቱ ድርጅት ሰራተኞች ላይ ስትፈጽም እንኳንስ የፀጥታው ምክር ቤት አጀንዳ አድርጎ ሊመክርበት ይቅርና ትንፍሽ ያለ አልነበረም። እናም ኢትዮጵያ ከተልእኮዋቸው ውጪ ባልተገባ ተግባር ውስጥ ተሰማርተው የነበሩ ሰባት የተ.መ.ድ ሰራተኞች ከአገር እንዲወጡ ያሳለፈችው ውሳኔ ከአሜሪካው ምን የለየው ነገር ቢኖር ነው የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ጠርቶ አካኪ ዘራፍ ማለቱ?
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በውይይቱ ላይ “የኢትዮጵያ ውሳኔ የተ.መ.ድን ህግ የተፃረረ ነው፣ ሰራተኞቹን የማባረር መብት የላትም” ማለታቸውም የአሜሪካን ጨምሮ የቀደሙት ታሪኮች ሳያውቁ ቀርተው ነው? ያስብላል። ድርጅቱ የተቋቋመባቸው መርሆዎች ሰብዓዊነት፣ እኩልነት፣ ሚዛናዊነት፣ ገለልተኝነት፣ ምክንያታዊነት እና ሌሎች መሰል የመርህ ምሶሶዎች ናቸው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የድርጅቱ ዋነኛ መርሆዎችን ወደጎን በማድረግ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ጉዳዮች ላይ እያተኮረ መጥቷል። ከዚህ ሻገር ሲልም በአገራት ውስጣዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ጣልቃ መግባት ዋና ስራው እየሆነ መጥቷል።
ኢትዮጵያም ከላይ የተጠቀሱትን የድርጅቱ መርሆዎች ባለመከበራቸው ብሎም ደህንነቷ እና ግዛታዊ አንድነት ላይ ስጋት ደቅነዋል ባለቻቸው የደርጅቱ ሰራተኞች የወሰደችው እርምጃ አንዳች የተለየ ነገር አለመኖሩን የመንግስታቱ ድርጅትም ይሁን መላው ዓለም የሚያውቀው ጉዳይ ነው።
እውነታው እንዲህ ሆኖ ሳለ በተ.መ.ድ ውስጥ አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ የመብት ተቆርቋሪ ነን ባይ አገራት ጉዳዩን ቀድሞ ከማጣራት ይልቅ የውሳኔው አስደንጋጭነት ላይ ትኩረት ያደረጉት ለምን ይሆን? ኢትዮጵያ ሰራተኞቹን ከሉዓላዊነት ጋር በማያያዝ ከሃገር እንዲወጡ አደረገች እንጂ አጠቃላይ ድርጅቱም ሆነ ኤጄንሲዎቹ በግዛቷ ውስጥ እንዳይንቀሳቀሱ አለማደረጓን ግልጽ አድርጋለች፤ በተባረሩት ሰራተኞች ምትክ ድርጅቱ ሌሎች ሰራተኞች እንዲልክም ጠይቃለች።
ጉዳዩ የሰብዓዊነት አለመሆኑንና ፖለቲካዊ ሴራ ያዘለ መሆኑን ቀድመው የተገነዘቡት ሩሲያ እና ቻይና በተወካዮቻቸው በኩል አቋማቸውን ግልጽ አድርገዋል። ዓለም አቀፍ ህጎችን በተፃረር መልኩ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚደረጉ ተናጥላዊ ውሳኔዎች ችግሩ ያባብሳል እንጂ መፍትሄ ሊሆን ስለማይችል አገራቸው እንደማትቀበለው በተ.መ.ድ የሩሲያ አምባሳደር አስረድተዋል። ችግሩ እልባት እንዲያገኝ ተ.መ.ድ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት ሊሰራ እንደሚገባ በማመን ሩሲያ አዲስ ለተመሰረተው የኢትዮጵያ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ይፋ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ በተ.መ.ድ ሰራተኞች ላይ ስለወሰደችው እርምጃ ለማንም ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት ባይጠበቅባትም በተባበሩት መንግስታት ዋና መስሪያ ቤት የኢትዮጵያ ቋሚ ወኪል በሆኑት አምባሳደር ታዬ አጽቀ ስላሴ በኩል ምላሽና ማብራርያ ሰጥታለች። አምባሳደር ታዬ የኢትዮጵያ እርምጃዎች ከሉዓላዊነትና ከህግ የበላይነት እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ህጎች፣ ከድርጅቱ ቻርተሮችና ከሞራል አኳያ ታይተው የተወሰኑ መሆናቸው አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በግዛታቸው ውስጥ በሰብአዊ አገልግሎት ድጋፍ ሽፋን የሚደረጉ የትኞቹንም ተግባራት በቅርበት የመከታተል ያልተሸራረፈ መብት እንዳላቸው በማስታወስ ጭምር።
አምባሳደር ታዬ ኢትዮጵያ እስካሁን በወሰደቻቸው እርምጃዎች የትኛውንም ዓለም አቀፍ ህግ እንዳልጣሰች ገልጸው የድርጅቱ ሰራተኞችም በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች ሁሉ የአገራትን ባህሎችና መተዳደሪያ ህግጋትን የማክበር ግዴታ እንዳለባቸው የመንግሥታቱ ድርጅት የመተዳደሪያ ደንብ ምዕራፍ 15 አንቀጽ 101 ቁጥር 3ን ዋቢ አድርገው አብራርተዋል።
ከኢትዮጵያ እንዲወጡ የተደረጉት የድርጅቱ ሰራተኞች የኢትዮጵያን ብቻም ሳይሆን የድርጅቱን መርሆዎች በተደጋጋሚ የጣሱ ከመሆናቸውም በላይ የኢትዮጵያ መንግስት ህጋዊና አስተዳደራዊ ተግባራት እንዳይሳኩ የማደናቀፍ ዓላማ ነበራቸው። ከተሰማሩበት የሰብዓዊ እርዳታ ስርጭት ሥራ ውጭም ከአሸባሪ ድርጅቱ ጋር ግንኙነት በመፍጠር የተዛቡ መረጃዎችና ሃሰተኛ እንዲሁም የተጋነኑ አሃዛዊ ሪፖርቶችን ሲያሰራጩ የነበሩ ናቸው። ያልሞቱ ሰዎችን በረሃብ ሞተዋል በማለት የሀሰት ምስክርነት መስጠት፣ ለሰብዓዊ እርዳታ ብቻ የተፈቀዱ የመገናኛ መሣሪያዎችን ለህወሓት ማቀበል፣ ህወሃት ተመልሶ መቐለ ከተማ ሲገባ ከቡድኑ ጋር ደስታቸውን ሲገልጹ የቆዩ ነበሩ።
ሰባቱ ሰራተኞች ለተቀጠሩባቸው ኤጄንሲዎች በተለያየ ጊዜ የስነ-ምግባር ማሻሻያ እንዲደረግ የሚያስችሉ መረጃዎችን ስትሰጥ ብትቆይም ግለሰቦቹ ከድርጅቱ እውቅና ውጭ አደገኛ የፍረጃ ቃላትን በመጠቀም በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና እንዲፈጠር በማለም ከአሸባሪው ቡድን ጋር ሴራ ማሴራቸውን ባለማቆማቸው ጉዳዩ ከአገሪቱ ሰላምና ደህንነት ጋር ቀጥተኛ ተቃርኖ ስለነበረው ኢትዮጵያ ውሳኔውን ገቢራዊ ለማድረግ ተገዳለች።
ሌሎች አገራት የተ.መ.ድ ሰራተኞችንና ዲፕሎማቶችን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ከሀገራቸው እንደሚያባርሩ ለማንም ግልጽ ቢሆንም የጸጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን አስመልክቶ ስብሰባ አድርጎ አያውቅም። በአንፃሩ ኢትዮጵያ ለወሰደችው መሰል እርምጃ ከድርጅቱ መርሆ ባፈነገጠ መልኩ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ መቀመጡ የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ እና ስብሰባ እንዲካሄድ ያስገደዱ አገራት ተወካዮች አሸባሪው የህወሓት ቡድን ህይወት እንዲዘራ ለማድረግ ምን ያህል በተወሳሰበ የሴራ ፖለቲካ ውስጥ መግባታቸውን ያመለክታል። ምንም እንኳ የሴራው አቀንቃኞች ያቀዱትን ለማሳካት አንገብጋቢ ስብሰባ ቢያደርጉም በራሽያ እና ቻይና በኩል በቀረበው ተቃውሞ ሴራው ከሽፏል።