ፍትሃዊነት የራቀው… - ኢዜአ አማርኛ
ፍትሃዊነት የራቀው…
ኢትዮጵያ ከሰሞኑ ከተልዕኮ ውጪ ሲንቀሳቀሱ የተገኙ 7 የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ድጋፍ ሰራተኞች ከሀገር እንዲወጡ በማድረጓ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት አንገብጋቢ ያለውን ስብሰባ አካሂዷል። የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ህግን እንደጣሰች ለማስረዳት ሞክረዋል። የአሜሪካ ተወካይን ጨምሮ አንዳንድ የምእራቡ ዓለም ሀገራት ተመሳሳይ ክስ ሰንዝረዋል። የምክር ቤቱን ስብሰባ አስገራሚ የሚያደርገው ደግሞ ተመሳሳይ እርምጃ የወሰዱ በርካታ አገራት እንዳሉ እየታወቀ የኢትዮጵያ ሲሆን ለምን ስብሰባ መቀመጥ እንዳስፈለገው ነው።
አሜሪካ እ.ኤ.አ በ2018 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ የሚሰሩ 12 የሩሲያ ዲፕሎማቶችን ጨምሮ 60 ዲፕሎማቶች አባራለች። ከሁለት ዓመታት በፊትም የኩባ ዜግነት ያላቸው ሁለት የተ.መ.ድ ሰራተኞች በአስቸኳይ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ማድረጓ አይዘነጋም። የትራምፕ አስተዳደር ሰራተኞቹን ለማባረር በምክንያትነት ያቀረበው ኩባውያን የተመድ ሰራተኞች አሜሪካን እየሰለሉ ነው የሚል ነበር።
እስራኤል እ.ኤ.አ በ2020 በሀገሪቱ ሲሰሩ ከነበሩ 12 የድርጅቱ ሰራተኞች መካከል ዘጠኙን ከተልዕኳቸው ውጪ ሲንቀሳቀሱ አግኝተናቸዋል በሚል ሀገር ለቀው እንዲወጡ አድርጋለች። እስራኤል ካሰናበተቻቸው የተመድ ሰራተኞች እና ሀላፊዎች መካከል የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር እና በእስራኤል የተመድ ሃለፊ የነበሩትን ጄምስ ሄይናንን ጨምሮ ዘጠኝ ሰራተኞች ይገኙበታል፡፡
ሀገራት ተመሳሳይ እርምጃ በወሰዱበት ጊዜ ምንም ያላለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኢትዮጵያ በወሰደችው እርምጃ ይህን ያህል ጩኸት ከድርጅቱ መሰማቱ የድርጅቱ ኢፍትሐዊነትን በገሃድ ያሳየ ነው። ጉዳዩም ፖለቲካዊ እንጂ ለሰብአዊነት ከመቆርቆር የመነጨ አለመሆኑን አሳይቷል። አሜሪካ እርምጃውን እኤአ በ2018 ከወሰደች በኋላ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ቃል አቀባይ የነበሩት ፈርሃን ሀቅ ጉዳዩን አስመልከተው በሰጡት መግለጫ አሜሪካንን ተጠያቂ የሚያደርግ ሳይሆን መብቷን ስለመጠቀሟ አንቀጽ ጠቅሰው ነበር እውቅና የሰጧት፡፡ ታዲያ መሰል እርምጃ በወሰደች ኢትዮጵያ ላይ ይህ ሁሉ ርብርብ ለምን?
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፍትሃዊነት መርህ መሰረት በሀገራት የሚወሰዱ ተመሳሳይ እርምጃዎችን በተመለከተ ከድርጅቱ የሚሰጡ ውሳኔዎች እንደየሀገራቱ ባህሪ እና ግዝፈት የሚመሰረቱ ሳይሆን ሁሉንም ሀገራት በእኩልነት በማየት የሚወሰን ነው። አሁን እየታየ ያለው ግን ኢትዮጵያ የወሰደችውን መሰል እርምጃ “ተገቢነት የለውም ውሳኔዋንም መቀልበስ አለባት” የሚል ንግግር ዋና ጸሐፊው አሰምተዋል። የትኛውንም ሀገር ያልጠየቁትን የሰነድ ማስረጃም ነው ኢትዮጵያ እንድታቀርብ ለማስገደድ የሞከሩት።
ሀገራት ባላቸው ሉኣላዊ መብት ከተልእኮአቸው ያፈነገጠ ተግባር ሲፈጽሙ በ24 ሰዓት ውስጥ እንዲወጡ ያደርጋሉ። አሜሪካ ዲፕሎማቶችን ከሀገር ስታባርር ስጋት አለን በሚል ምክንያት ብቻ መሆኑን በርካታ አስረጂዎች አሉ። በዚህ ወቅት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጠየቁት ምንም አይነት ተጨማሪ ማብራሪያም ይሁን ሰነድ አልነበረም፡፡ ታዲያ የኢትዮጵያ እርምጃ እና ውሳኔ በሰነድ አልተደገፈም መባሉ ጠያቂዎቹ ያላቸው ጭፍን የፖለቲካ ፍላጎት ለማሳካት ስለመሆኑ የሚያሳይ ነው።