አዲሱ ምዕራፍ የራሳችንን ጉዳይ በራሳችን እንደምንፈጽም ያሳየ ነው

59

አዲስ አበባ፤ መስከረም 28 / 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የተጀመረው አዲስ ምዕራፍ የራሳችንን ጉዳይ በራሳችን እንደምንፈጽም ያሳየ ነው ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል የጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ሄኖክ ስዩም ተናገሩ።

አዲሱ ምዕራፍ ጉዳዮቻችንን በራሳችን አቅም መከወን እንደምንችል የታየበት ነው ያሉት ዶክተር ሔኖክ፤

በሁሉም መስክ ከውጭ አገራት ጫና ለመላቀቅና ራሳችንን ለመቻል ጠንክረን የምንሰራበትም ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን አቅማችንን በማሳደግ ሠላማችንን ማረጋገጥ፣ በምግብ ራስን መቻል ለዚህም በሁሉም መስክ ጠንክረን መስራት ይኖርብናል ነው ያሉት።

በዚህ አዲስ ምዕራፍ ኢትዮጵያዊያን የራሳችንን መንግስት በራሳችን የምንመርጥ፣ የራሳችንን ጉዳይ ራሳችን የምንፈታ ሉዓላዊ አገር መሆናችንን አሳይተናልም ብለዋል።

ሉዓላዊነታችንን ለማንም አሳልፈን የማንሰጥ ነን፤ ይህን ጥሶ ለሚመጣ ደግሞ የእጁን አግኝቶ እንደሚመለስ ታሪክ ምስክር ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ከድህነት ለመውጣትና ሉዓላዊነታችንን ሙሉ ለማድረግ ጠንክረን መስራት ያስፈጋል ብለዋል።

"ኢትዮጵያ ሉዓላዊት አገር ናት፣ ሉዓላዊ መንግስትም አላት" ያሉት ዶክተር ሔኖክ ይህ ሕዝብና መንግስት ሁሉንም በራሱ የማድረግ ሙሉ አቅም አለው ብለዋል።


የአሜሪካ መንግስትና ተባባሪዎቹ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመዳፈር ጫና የማድረግና እጅ የመጠምዘዝ ሙከራ ተቀባይነት እንደሌለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ማሳየቱንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም