ቀጥታ፡

የአሸባሪ ቡድኑ ጥቃት ትዮጵያዊያን ቀፎው እንደተነካበት ንብ በጋራ እንዲተሙ አድርጓል

መስከረም 28/2014(ኢዜአ) የአሸባሪ ቡድኑ ጥቃት ኢትዮጵያዊያን ቀፎው እንደተነካበት ንብ በጋራ እንዲተሙ አድርጓል ሲሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ተናገሩ።
 በአገሩ ሉዓላዊነት የማይደራደረው የአፋር ሕዝብ ራሱን በምሽግ እንዳለ ወታደር አሳምኖ የጠላትን እንቅስቃሴ ለመከላከል በተጠንቀቅ ላይ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ ይህን ያሉት አቶ ምህረተአብ ሙሉጌታ የተባሉ ባለሀብት በአፋር ክልል ችግር ለደረሰባቸው ዜጎች ያደረጉትን የግማሽ ሚሊዮን ብር ድጋፍ በተረከቡበት ወቅት ነው።

አቶ ምህረተአብ ድጋፉን ያደረጉት፤ ኢትዮጵያ ያጋጠማትን የውስጥና የውጭ ፈተናዎች ለመቋቋም ለሚታገሉ የክልሉ ልዩ ኃይልና ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ያላቸውን ክብር ለማሳየት መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደረው የአፋር ሕዝብ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጋር በመቀናጀት ባደረገው ተጋድሎ አሸባሪው የህወሓት ቡድን የጅቡቲን መስመር ለመዝጋት ያደረገውን እንቅስቃሴ ማክሸፉን አድንቀዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የውጭ ጠላቶች ከውስጥ ባንዳ ተላላኪዎቻቸው ጋር በመሆን ኢትዮጵያውያን አንድነት እንዳይኖራቸው የሐስት ትርክት የመፍጠር ዘመቻ ማካሔዳቸውንም ገልጸዋል።

"ኢትዮጵያውያን አንድነትና ሕብረት ካለን ከእኛ አልፈን ለአፍሪካ ጉልበት እንሆናለን" ያሉት አቶ ምህረተአብ፤ ይህን የፈተና ጊዜ ተጋግዘን ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ መውሰድ ይገባል ነው ያሉት።

በቀጣይም በሌሎች አካባቢዎች በሸብር ቡድኑ ለተፈናቀሉ ወገኖች እቅማቸው በፈቀደ መጠን ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

ባለሃብቱ ከዚህ ቀደም ለመከላከያ ሠራዊት በጥሬ ገንዘብና በቁሳቁስ በጥቅሉ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ  ማድረጋቸው ተወስቷል።

የአፋር ክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ ወጣቱ ባለሃብት በአዲሱ መንግስት ምስረታ ማግስት ለክልሉ ሕዝብ ድጋፍ በማድረግ የዜግነት ግዴታውን መወጣቱን አድንቀዋል።

በአሁኑ ወቅት ግለሰቦችና ተቋማት ለችግር የክልሉ ነዋሪዎችን ለመርዳት እያደረጉት ላለው ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

"የኢትዮጵያ ትልቁ ወዳጇ በውጭ አካላት ላይ መንጠልጠል ሳይሆን ውስጣዊ አቅሟ ነው" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ትልቁ ጠላቷ ደግሞ ድክመቷ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

አቅም በጠነከረ ቁጥር ወዳጅ ይበዛል፤ ኢትዮጵያ ትልቅ አቅም ስላላት ዛሬ ጠላቶቿ መስለው የሚታዩት ሁሉ ነገ ጠንካራ ኢትዮጵያ ስትፈጠር ወዳጅ እንሁን ብለው መምጣቸው አይቀሬ መሆኑን አንስተዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያን የመምራት ዕድል ቢያገኝም ራሱን ነፃ አውጪ አድርጎ ሲጠራ እንደቆየ ያስታወሱት አቶ አወል፤ ሴረኛው ቡድን የኢትዮጵያዊ ወዳጅ ለመምሰል ቢጥርም  እውነታው ግን የአገሪቷ ጠላት መሆኑን በተግባር አረጋግጧል ብለዋል።

በስልጣን ዘመኑም የጸጥታ መዋቅሩን ከላይ እስከታች በመቆጣጠር ኢትዮጵያን እየቦረቦረና እየዘረፈ መቆየቱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን እንዴት እንደሚያፈርስ ሲሰራ መቆየቱንና የዕቅዱም ሰነድ መጋለጡን የጠቀሱት አቶ አወል፤ ሁሉም ዜጋ ቡድኑ የኢትዮጵያ ጠላት መሆኑን መረዳት ይገባዋል ብለዋል።

ስለሆነም "ጠላቱን በሚገባ ያልለየ የጠላት ቀለብ መሆኑ አይቀርምና፤ ኢትዮጵያዊያን ጠላትን መለየት አለብን" ብለዋል። 

ቡድኑ ወጣቶችን እየጨረሰ የ'አሸንፈናል' የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እየነዛ ቢሆንም ሲያልመው ከነበረው አፋር ምድር ተሸንፎ እንዲወጣ መደረጉን ገልፀዋል። 

ቡድኑ ክልሉን ተጠቅሞ ኢትዮጵያን ለማፍረስ አልሞ የነበረ ቢሆንም በሕዝቡና በመከላከያ ሠራዊቱ የጋራ ትግል ሕልሙ በአጭር እንዲቀጭ መደረጉን ተናግረዋል።

አፋር በታሪኩ በኢትዮጵያዊነቱ፣ በአገሩ አንድነትና ሕልውና ተደራድሮ አያውቅም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለኢትዮ-ጅቡቲ መስመር ጥበቃ ራሳችንን ምሽግ ላይ እንደተቀመጠ ወታደር አሳምነናል ብለዋል።

የአሸባሪ ቡድኑ ጥቃት ኢትዮጵያዊያን ቀፎው እንደተነካበት ንብ በጋራ እንዲተሙ አድርጓል ያሉት አቶ አወል ቡድኑ እንዲደመሰስ ጥረታችን ይቀጥላል፤ አንዘናጋም ብለዋል።

መላው የአገሪቷ ሕዝብም የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ለአገሩ ዘብ ለቆመው የመከላከያ ሠራዊት  የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በአገሪቷ ላይ የጥፋት ተግባር እየፈፀመ ያለው የሽብር ኃይል እንዲደመሰስ የክልሉ መንግስት እያደረገ ያለውን ትብብር ይቀጥላል፤ አንዘናጋም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም