ቀጥታ፡

በሚኒስትሮች ሹመት ተፎካካሪ ፓርቲዎች መካተታቸው የሀገሪቱን እድገትና አንድነት ያጠናክራል

ጋምቤላ ፤ መስከረም 28/2014(ኢዜአ) በተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የሚኒስትሮች ሹመት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካተታቸው የሀገሪቱን ዕድገትና የሕዝቦችን አንድነት እንደሚያጠናክር የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ሹመቱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለአገራቸው  ሰላምና ብልጽግና  በአንድነት እንዲቆሙ  ነው ነዋሪዎቹ አሰተያየታቸውን ለኢዜአ  የገለጹት።

ከነዋሪዎቹ መካከል ኮማንደር ኡማን ኡጋላ እንዳሉት፤ በፓርላማ ደረጃ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ባካተተ መልኩ የተሰጠው ሹመት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን  ለአፍሪካ ጭምር ተምሳሌት ነው።

ከአሁን በፊት በነበሩት አምስት የምርጫ ወቅቶች ባልተለመደ መልኩ በአብላጫ ድ ምጽ አሸንፎ መንግሥት የመሰረተው ብልጽግና ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በአስፈፃሚው አካላት እንዲካተቱ ማድረጉ ሀገራዊ አንድነትን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።

በአስፈፃሚው አካላት የተካተቱ ፓርቲዎች በምርጫ ወቅት ከመንግሥት ጎን በመሆን ለሀገርና ሕዝብ ብሔራዊ ጥቅም መከበር ሲሰሩ እንደነበር ጠቁመው፤ ይህም ለአገር ሰላምና ልማት ተባብረው እንደሚሰሩ ያሳያል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊሾሙ ቀርቶ በሀገር ውስጥ በሰላም የማይኖርበት ሁኔታ እንደነበር በማስታወስ አስተያየታቸውን የሰጡት ደግሞ  አቶ ኒይና ኦኬሎ ናቸው።

አሁን ላይ ግን ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአስፈፃሚ አካላት እንዲካተቱ መደረጉ ታላቅ የፖለቲካ የለውጥ ምዕራፍ መሆኑንም አስረድተዋል።  

ሹመት የዳር ተመልካችነትንና ትችትን በመተው ለሀገር ሰላምና ብልጽግና በአንድነት እንዲቆም ያደርጋል ብለዋል።

ሚኒስትሮቹ ሀገሪቱ ያሉባትን በተለይም የሰላም፣ የኑሮ ውድነቱንና የሥራ አጥነት ችግሮች ይፈታሉ የሚል እምነት እንዳላቸውም ነው አቶ ኒይና የተናገሩት።

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ የቀድሞው የባህር ኃይል አባል አቶ ኡሞድ ኡሜት በበኩላቸው፤ ባለፉት 27 ዓመታት የነበረው የፖለቲካ መዋቅር ብሄርን መሰረት  ያደረገ ስለነበር  ግጭቶች ተበራክተው እንደቆዩ  ያስታውሳሉ።

አሁን ላይ ግን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማካተት የተካሄደው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሹመት የቀድሞውን መጥፎ ታሪክ በመሻር የልማትና የብልጽግና ጉዞውን የሚያፋጥን ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሚኒስትሮቹ ለሀገር እንዲሰሩ የሰጡት ማሳሰቢያ አንድነትን የሚያጠናክር መልዕክት ሆኖ እንዳገኙትም ጠቅሰዋል።

አዲሶቹ ሚኒስትሮችም ማሳሰቢያ በመቀበል የኢትዮጵያን ሕዝብ በእኩልነትና ታማኝነት በመስራት ዘላቂ ሰላምና ልማት እንደሚያመጡ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡለትን የ22 ሚኒስትሮችን ሹመት ማጽደቁ የሚታወስ ሲሆን፤ ከመካከላቸው ሶስት የተፎካካሪ ፖለቲካ  ፓርቲዎች  አመራሮች ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም