አዲሱ መንግስት አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አሰራሮችን መተግበር ይጠበቅበታል - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ መንግስት አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አሰራሮችን መተግበር ይጠበቅበታል
መስከረም 28/2014 (ኢዜአ) አዲስ የተመሰረተው መንግስት አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርጉና አካታች የሆኑ አሰራሮችን መተግበር እንደሚጠበቅበት የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ገለጸ።
አዲሱ መንግስት የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች በመፍታት ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና ለማድረስ የሚያስችሉ ጠንካራ ስራዎችን እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መናገራቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አባይነህ ጉጆ አዲሱ መንግስት የአካል ጉዳተኞችን መሰረታዊ ችግሮች በመፍታት ረገድ ከበፊቱ የተሻለ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ከዚህ አኳያ በየ ደረጃው ያለው የአዲሱ መንግሥት መዋቅር በማህበራዊ፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚያዊ መስኮች በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች አካል ጉዳተኞችን በማካተት ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይጠበቅበታል ነው ያሉት።
አካል ጉዳተኞች ከሙስናና ብልሹ አሰራር የጸዳች እንዲሁም ደህንነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን እንደሚሹም ነው የገለጹት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሙስና የፀዱ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ኢትዮጵያን ከድህነት ማላቀቅ የመጪው ዘመን የቤት ስራ ሊሆን እንደሚገባ ለካቢኔ አባላቶች ማሳሰባቸውንም አስታውሰዋል።
ከዚህ አኳያ አካል ጉዳተኞች መስራት የሚችሉ፣ ዕውቀትና አቅም ያላቸው መሆኑን አምኖ የሚቀበልና አሳታፊ የሆነ የመንግሥት መዋቅር ሊኖር ይገባል ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አባይነህ።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የአካል ጉዳተኞች ረቂቅ አዋጅ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው፤ አዋጁ በአዲሱ መንግስት ጸድቆ ተግባራዊ ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
የአዋጁ ተግባራዊነት ለአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው በመግለጽ።
አካል ጉዳተኞችን በአመራርና በፖለቲካ ተሳትፎ ማብቃት እንዲሁም የዘርፉን ማህበራት መደገፍና ማጠናከር ከአዲሱ መንግስት የሚጠበቅ ተግባር መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል።
በየደረጃው ባሉ የአዲሱ መንግስት መዋቅሮች አካል ጉዳተኞችን ወደ አመራርነት ለማምጣት የሚያስችሉ ስራዎች ታሳቢ እንዲደረጉም ነው የጠየቁት።
አካል ጉዳተኞች ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ መካከል 17 ነጥብ 6 በመቶ ድርሻ የሚይዙ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል የትምህርት እድል የሚያገኙት ከ5 በመቶ እንደማበልጡ የትምህርት ሚኒስቴር ሪፖርት ያሳያል፡፡