ፋሲል ከነማና ኢትዮጵያ ቡና ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚሆን የገቢ ማሰባሰቢያ ግጥሚያ አካሔዱ - ኢዜአ አማርኛ
ፋሲል ከነማና ኢትዮጵያ ቡና ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚሆን የገቢ ማሰባሰቢያ ግጥሚያ አካሔዱ
ባህር ዳር፤ መስከረም 27/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ለማሰባሰብ ዓላማ ያደረገው የፋሲል ከነማና የኢትዮጵያ ቡና የእግር ኳስ ቡድኖች ጨዋታ በባህር ዳር ዓለም ዓቀፍ ስታዲየም ተካሔደ
በወዳጅነት ጨዋታውም ፋሲል ከነማ ኢትዮጰያ ቡናን 2 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
የባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ በዕለቱ እንደተናገሩት ከቤት ንብረታቸው የተፋናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት በጎ ፈቃደኞች እያደረጉ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው።
ይህ የበጎነት እንዲሁም የሰብዓዊ ድጋፍና እገዛ ትልቅ የህሊና ስንቅ ከመሆኑም በላይ በአስቸጋሪ ወቅት ወገን ለወገን ያለውን መረዳዳት በተግባር የሚያሳይ እንደሆነም ገልፀዋል።
በቀጣይም ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳት ያስችል ዘንድም ገቢ ማሰብሰቢያ ፕሮግራሞች በስፋት እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል እግር ኳስ ፌደሬሽን ፀሃፊ እና የውድድሩ አዘጋጅ አቶ መኳንንት ደነቀው በበኩላቸው አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአማራ ክልል በፈፀመው ወረራ ዘርፈ ብዙ ጉዳት አድርሷል።
በዚህም ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ድጋፍ ለማድረግ መንግስትና ህብረተሰቡ ሰፊ እንቅስቃሴ እያከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።
በወቅታዊ ሁኔታው ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለማገዝም የአማራ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ጋር በመቀናጀት የገቢ ማሰባሰቢያ ስፖርታዊ ውድድሩ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።
የዛሬውን ጨምሮ በቀጣይ በሚደረጉ የስፖርታዊ ውድድሮች ሙሉ በሙሉ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚሆን ከ3 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ገልጸዋል።
የፊታችን እሁድ የአዲስ አበባ የሲቲ ካፕ የፍፃሜ ጨዋታም በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም እንዲካሄድ የተወሰነ መሆኑን ጠቅሰው፤ የባህር ዳርና አካባቢው ነዋሪዎች ጨዋታውን በመታደም አጋርነታቸውን እንዲያሳዩም ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ ጨዋታ ሰብዓዊነትን ዓላማ ያደረገ በመሆኑ ሁለቱም ቡድኖች አሸናፊ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ለቡድኖች ታላቅ ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም እግር የኳስ ግጥሚያን ጨምሮ የሩጫ ውድድሮች እንደሚከናወኑም አመልክተዋል።
የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድን አምበል አምሳሉ ጥላሁን በበኩሉ ጨዋታው ለተፈናቃይ ወገኖች ገቢ ማሰባሰቢያ በመሆኑ እንዳስደሰተው ገልጿል።
ለዚህ በጎ ዓላማ በስታዲም በመታደም ጨዋታውን የተመለከቱ ደጋፊዎችን አመስግኖ፤ ሌሎች የእግር ኳስ ክለቦችም በመሰል የበጎ ተግባር ዓላማ እንዲሳተፉ አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ተጫዋች የሆነው ሃይሌ ገብረተንሳይ በበኩሉ በዚህ የበጎ ተግባር ስራ ለሚውለው የእግር ኳስ ጨዋታ በመሳተፉ ኩራት እንደተሰማው ተናግሯል።
በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በተካሄደው የወዳጅነት ጨዋታውም ፋሲል ከነማ ኢትዮጰያ ቡናን 2 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።