ቀጥታ፡

በ42ኛ ክፍለ ጦር የ3ኛ ሬጅመንት አባላት ለሕዳሴው ግድብ የ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ

መተማ/ጎንደር ግንቦት 8/2010 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ታች አርማጭሆ ወረዳ የሚገኘው 42ኛ ክፍለ ጦር የ3ኛ ሬጅመንት አባላት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዢ ፈጸሙ፡፡ የሕዳሴ ሰላም ዋንጫ በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ ከተማ በክፈለጦሩ ከ3ኛ ሬጅመንት ወደለ4ኛው ሬጅመንት ርክክብ ተደርጓል፡፡ የታች አርማጭሆ ወረዳ ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ካሳሁን ይላል ለኢዜአ እንደተናገሩት አባላቱ የቦንድ ግዢውን የፈጸሙት በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ ሲዘዋወር የቆየውን የሕዳሴ ግድብ የሰላም ዋንጫ ቆይታ ምክንያት በማድረግ ነው፡፡ በቦንድ ግዢ ስነ-ስርአቱ ላይ የ3ኛ ሬጅመንት አባል የሆነው ሃምሳ አለቃ ሰጠኝ ካሳዬ በግሉ የ160 ሺህ ብር ቦንድ በመግዛት የሠራዊቱ ግንባር ቀደም አርአያ መሆን እንደቻለም አቶ ካሳሁን ተናግረዋል፡፡ የሰላም ዋንጫው በመከላከያ ሠራዊቱ የ3ኛ ሬጅመንት የነበረውን የቆይታ ጊዜ በማጠናቀቅ በትናንትናው እለት በመተማ ወረዳ ወደሚገኘው የ42ኛ ክፍለ ጦር 4ኛ ሬጅመንት አሸኛኘት ተደርጎለታል፡፡ የሕዳሴ ሰላም ዋንጫ በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ ከተማ ለ4ኛው ሬጅመንት ትናንት ርክክብ ሲደረግ በመከላከያ ሠራዊት አባላትና በከተማው ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡ በርክክቡ ወቅት የ42ኛ ክፍለ ጦር ምከትል አዛዥ ኮሌኔል ተሾመ ተክለሃይማኖት እንዳሉት የዋንጫው ትልቁ ዓላማ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠርና ለግድቡ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡ "የሠራዊ አባላቱ የአገራቸውን ዳር ድንበር ከጠላት ከመጠበቅ በለፈ በዚህ ታራካዊ ቀን ቦንድ በመግዛት ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድጋፍ ማድረጋቸው ድርብ  ኩራት ነው" ሲሉም ገልጸዋል። ሰራዊቱ ሰላምን ከማስከበር ጎን ለጎን በልማት ግንባር ቀደም ተሳታፊ በመሆኑ የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ የሚያደርገውን የገንዘብ  ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡ በ42ኛ ክፈለጦር የ4ኛ ሬጅመንት ምክትል አዛዥ ኮለኔል ሙሀመድ ሙሳ በበኩላቸው " ሠራዊቱ ለአገሩ ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የማይመለስ ሕይወቱንም ይሰጣል" ብለዋል፡፡ ቀደም ሲል ለስድስት ተከታታይ ዓመታት የወር ደመወዛቸውን ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጋቸውን የገለጹት ኮለኔል ሙሀመድ፣ በተያዘው  በጀት ዓመትም  የ20 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል። ሌላኛው የሬጅመንቱ አባል ሻምበል ባሻ ታደሰ አበበ እንደገለፁት በዚህ አመት የ10ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን አስታውሰው፣ በዋንጫ ርክክቡ ወቅት የ30 ሺህ ብር ዋጋ ያለው ቦንድ መግዛታቸውን አመልክተዋል፡፡ ወታደር ስምዖን ጎልቻ በበኩሉ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ  ግድብ የአቅሙን ድጋፍ በማድረግ የራሱ አሻራ ለማሳረፍ ጽኑ ፍላጎት እንዳለው ነው የተናገረው። ለዋንጫው አቀባበል በተደረገበት ስነሰርአት ላይ የ4ኛ ሬጅመንት አባላት ከ650 ሺህ ብር በላይ ዋጋ ያለው የቦንድ ግዥ መፈጸማቸው ተገልጿል። በሬጅመንቱ " ለአባይ ግድባችን እስከደም ጠብታችን!!" የሚል መሪ ሃሳብ ቦንድ እየተሸጠ ሲሆን ይህም ለሦስት ቀናት እንደሚቆይ ታውቋል። በሕዳሴው ግድብ የሰላም ዋንጫ አቀባበል ስነ ስርዓት ላይ የሬጅምንቱ አባላት፣ የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም