ተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች በካቢኔ ውስጥ መካተታቸው በፖለቲካ ልዩነት ለዘመናት የዘለቀውን መጠፋፋት የሚያስቀር ነው - ኢዜአ አማርኛ
ተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች በካቢኔ ውስጥ መካተታቸው በፖለቲካ ልዩነት ለዘመናት የዘለቀውን መጠፋፋት የሚያስቀር ነው
መተማ፤ መስከረም 27/2014 (ኢዜአ) በጠቅላይ ሚንስትሩ የካቢኔ ሹመት የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች መካተታቸው በፖለቲካ ልዩነት ለዘመናት የዘለቀውን መጠፋፋት የሚያስቀር መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ።
አዲስ የተመሰረተው መንግስት የሀገርና የህዝብ ጥቅም ያስቀደመ መሆኑ ተመልክቷል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ/አብን/ የምዕራብ ጎንደር ዞን ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሰብሳቢ አቶ በላይነህ ሲሳይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አዲስ የተመሰረተው መንግስት የኢትዮጵያን ችግሮች ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን ያሳየ ነው።
ከዚህ በፊት የተለየ የፖለቲካ አመለካከትና አስተሳሰብ ያላቸው ግለሰቦች የሚገደሉበት፣ የሚሳደዱበት እና በግፍ ታስረው የሚሰቃዩበት ጊዜ እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ላይ በፌደራል መንግስት በሚኒስትርነት፣በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድርና በክልሎች በቢሮ ሃላፊነት የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን መሾም መቻሉ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።
የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትና አመራሮች በሀገር ጉዳይ ላይ ይበጃል የሚሉትን ሃሳብ በነጻነትና በግልጸኝነት ከማራመድ ባሻገር በቅንነትና ታማኝነት ሀገራቸውን የሚያገለግሉበት እድል መፈጠሩ መልካም ጅምር መሆኑን ጠቁመዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ መስራታቸው የህዝቡን አንድነት በማጠናከር ድህነት ላይ በጋራ ለመዝመት የሚያስችል ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ/ኢዜማ/ ፓርቲ የመተማ ወረዳ ሊቀመንበር አቶ ተሾመ ሞላ በበኩላቸው፤ በየደረጃው በተሰጠው ሹመት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካተታቸው አዲስ ልምምድን የፈጠረ ነው ብለዋል።
እስካሁን የነበረውን የገዥው ፓርቲ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ተግባራት ከመተቼት፣ ከመጠየቅና ከማጣጣል በመውጣት የጋራ ሃላፊነት ለመውሰድ እንደሚስችል አስረድተዋል።
''አዲስ የተመሰረተው መንግስት ኢትዮጵያዊያን በአሸባሪው ህወሓት አገዛዝ የተዘራውን የጥላቻ፣ የመለያየትና የዘር ፖለቲካ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ነቅለው የሚጥሉበት ጊዜ መምጣቱን የሚያረጋግጥ ነው'' ብለዋል።
በመተባበር መንፈስ ለሀገር እድገት የበኩላቸውን ሚና እንደሚጫወቱ ገልጸዋል።
አዲሱ መንግስት በህዝብ ድምጽ ያገኘውን ስልጣን ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ማጋራቱ አገር አሻግራለሁ ብሎ ለህዝብ የገባውን ቃል በተግባር ያረጋገጠበት ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ሰብሳቢ አቶ ገንብራቸው ጫኔ ናቸው።
"ሁሉም ፖለቲከኛ ለሀገርና ህዝብ በጋራ የሚሰራበት ሁኔታ ተፈጥሯል" ያሉት ሰብሳቢው ፤ ሁሉም አካላት የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ወደ ውጤት ለመቀየር መረባበር እንዳለባቸው አመልክተዋል።
አዲስ የተመሰረተው መንግስት የሀገርና ህዝብ ጥቅም ያስቀደመ መሆኑን ገልጸው፤ በጋራ ሰርቶ ሀገርን ለማሳደግ የሁላችንም ድርሻ ነው ያሉት።
ትናንት በተካሄደው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የካቢኔ ሹመት የኢዜማ፣ የአብንና የኦነግ አመራሮች ሚንስትር ሆነው መሾማቸው በወቅቱ ተገልጿል።