ቀጥታ፡

ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን

አዲስ አበባ መስከረም 27/2014 (ኢዜአ) ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክርቤት አባላት ገለጹ።

የምክር ቤቱ አባላት "ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ መቼም የትም በምንም" የሚለውን አገራዊ ጥሪ በመቀበል ለመከላከያ ሠራዊቱ ደም ለግሰዋል።

የምክር ቤት አባላት በዚህን ወቅት ሠራዊቱን በገንዘብና እውቀት ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ አለባቸው ደሳለኝ ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም ለመከላከያ ሠራዊቱ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል።

ምክር ቤቱ ስድስት ፕሮጀክቶች ይዞ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን ጠቅሰው፤  የደም ልገሳ  መርሀ-ግብሩ የፕሮጀክቱ አንዱ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ከሠራዊቱ  ጋር በደም የተሳሰረ ወገናዊ ፍቅርና አክብሮት እንዳለን ለመግለጽ ነው ብለዋል።

የምክር ቤቱ አባላት ዳያስፖራዎች በየትኛውም ጊዜና ቦታ ለሠራዊቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

የመከላከያ ደም ባንክ ዳይሬክተር ዶክተር ሻምበል ብርሀኑ ካሳዬ በበኩላቸው ህብረተሰብ ደም ከመለገስ ጀምሮ ለሠራዊቱ እያደረገው ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

ድጋፉ ለሠራዊቱ የሞራል ስንቅ መሆኑን ገልጸው፤ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በተለይ የደም ልገሳ መርሃ ግብር በዘመቻ መልክ ተከናውኖ የሚቆም ሳይሆን ቀጣይነት ያለው ተግባር ሊሆን እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

ነዋሪነታቸው በኖርዌይ የሆነው ወይዘሮ ኢትዮጵያ አለማየሁም፤ የደም ልገሳ መርሃ ግብሩ ከሠራዊቱ ጎን መቆማቸውን ለመግለጽ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም የምክር ቤቱ አባላት ሠራዊቱን በገንዘብ፣ በጉልበትና በእውቀት ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በደም ልገሳ መርሃ ግብሩ በመሳተፋቸው መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ ነዋሪነታቸው በአሜሪካ የሆኑት አቶ በፍቃዱ ተረፈ ናቸው።

የዳያስፖራ ማህበረሰብ ከአዲሱ መንግስት ጋር በመቀናጀት ሀገሩን ከፍ ለማድረግ የበኩሉን ሚና እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት በመስከረም 2013 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን፤ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎችን የያዘ ነው።

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ በመገንባት፣ በልማትና በትውልድ ቀረጻ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ይሰራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም