ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ተቀባይነት የለውም

መስከረም 27/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ተቀባይነት የለውም ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለፁ፡፡

አቶ ደመቀ በእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዩ ልዑክ አምባሳደር ባርሊ ሻሮን ከተመራው የእስራኤል ከፍተኛ የመንግስት የልዑካን ቡድን አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት በመከባበርና በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን በማውሳት፤ ይህንን ምቹ ሁኔታም በሀገራቱ በኢኮኖሚ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር መጠቀም አንደሚያስፈልግ አቶ ደመቀ ጠቁመዋል።

አክለውም በግብርና ምርታማነት፣ አቅም ግንባታ፣ በሰላም እና ደህንነት ዘርፎች የጋራ ትብብሮች እንዲጠናከሩ በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ፍላጎት ገልጸዋል። የኢትዮጵያን ህዝብ ይሁንታ ያገኘ አዲስ መንግስት መመስረቱን አስመልክቶም ለልዑካን ቡድኑ አባላት አቶ ደመቀ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በሌላ በኩል በመሬት ላይ ካለው ነባራዊ እውነታ በተጻረረ ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ያልተገባ የውጪ ጫና ለመቋቋም ኢትዮጵያ ለምታደርገው ጥረት እስራኤል ድጋፍ እንድትሰጥ አቶ ደመቀ ጠይቀዋል፡፡

አክለውም በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጸዋል። በአንጻሩ የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ተባብሮ ለመስራት ያለውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል፡፡

አምባሳደር ባርሊ ሻሮን በበካላቸው ለተደረገላቸው ገለጻ አመስግነው፣ መረጃውን ለእስራኤል መንግስት እንደሚያስተላልፉ ጠቁመዋል፡፡አያይዘውም አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ ወዳጅነት አጠናክራ እንደምታስቀጥል ማረጋገጣቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም