ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷንና የግዛት አንድነቷን ለማስጠበቅ የማንንም ፈቃድ አትጠይቅም - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷንና የግዛት አንድነቷን ለማስጠበቅ የማንንም ፈቃድ አትጠይቅም
አዲስ አበባ፣ መስከረም 27/2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷንና የግዛት አንድነቷን ለማስጠበቅ የማንንም ፈቃድ መጠየቅ የማይገባት መሆኑን ምሁራን ገለጹ።
የተመድ የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ታላላቅ ኃላፊነቶች እያሉበት በኢትዮጵያ ጉዳይ በአጭር ጊዜ ይህን ሁሉ ስብሰባ ማድረጉ የሚያሳዝን ነው ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ተከታታይ ውይይቶችን እያደረገ፣ ውይይቶቹም ያለ ስምምነት እየተበተኑ ይገኛሉ።
ምክር ቤቱ ትናንት ሌሊት ባደረገው ስብሰባም በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታና ከኢትዮጵያ እንዲወጡ የተደረጉ የተመድ ሰራተኞች ዙሪያ ውይይት አድርጓል።
በዚሁ ጉዳይ ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን የምክር ቤቱ ትልቁ ኃላፊነት የዓለም ሰላም እንዳይናጋ መጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል።
ሆኖም ምክር ቤቱ ይህን የሚያክል ትልቅ ኃላፊነት እያለበት በኢትዮዮጵያ ጉዳይ ተደጋጋሚ ስብሰባ ማድረጉ የሚያሳዝን መሆኑን ገልጸዋል።
ድርጊቱ የተባበሩት መንግስታት የተቋቋመበትን ዓላማና ድርጅቱን ጭምር ዝቅ የሚያደርግ እንደሆነም አንስተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሃኑ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷንና የግዛት አንድነቷን ለማስጠበቅ የማንንም ፈቃድ አትጠይቅም፤ ልትጠይቅም አይገባትም።
በሰሜኑ የአገሪቷ አቅጣጫ የገጠማትን ችግርም በራሷ መንገድ መወጣት ትችላለች፤ ይህንንም የተመድ ሰዎች ያውቁታል ብለዋል።
በተመድ ሽፋን የአገር ሉላዊነትን ሊዳፈሩ የሚችሉ ተግባራትን የሚፈጸሙ ግለሰቦች ሲያጋጥሙም የማባረር ሙሉ መብት አላት ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ እንደ አንድ ሉዓላዊ አገር ለደህንነት፣ ለሰላም ያሰጋኛል ያለችውን እንቅስቃሴ መከታተልና እርምጃ የመውሰድ መብት አላት ብለዋል።
''አይደለም ተጨባጭ ማስረጃ ተገኝቶባቸው ይቅርና በጥርጣሬ ብቻ ከአገር እንዲወጡ ማድረግ ይቻላል'' ይላሉ ፕሮፌሰር ካሳሁን።
ይህ የተመድና ሌሎች ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች ሰራተኞችን ብቻ ሳይሆን ዲፕሎማቶችን ጭምር ሊያካትት የሚችል እንደሆነ ነው ያነሱት።
ኢትዮጵያ መብት እንደሌላት አድርጎ ከማቅረብ ይልቅ ተመድ ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራርቦ ቢነጋገር የተሻለ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ተገቢነት በሌለው ድርጊት ውስጥ የተገኙ ሰራተኞች እንዲወጡ ነው እንጂ ያደረገው ድርጅቶቹ ስራ እንዳይሰሩ አላለም፣ ይህም ሊታወቅ ይገባል ብለዋል።
አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን የሚዳፈሩ የጣልቃ ገብነት እንቅስቃሴዎችን መከታተልና መመከቱን መቀጠል እንዳለባት አሳስበዋል።
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህሩ ዶክተር ተስፋዬ አባተ፤ ምክር ቤቱ ለዓለም የጸጥታ ስጋት ይሆናል ባለው ጉዳይ ላይ የመወያየት መብት አለው ይላሉ።
ሆኖም ግን ኢትዮጵያን የገጠማት የውስጥ ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን ችግሩን በራሷ እንድትፈታ ከማገዝ ይልቅ አጀንዳ አድርጎት መቆየቱ ተገቢ አይደለም ባይ ናቸው።
ይህም በመሆኑ የምክር ቤቱ አባላት በኢትዮጵያ ላይ አጀንዳ ሆነው በሚቀርቡት ጉዳዮች ላይ ሳይግባባ የሚበተነው ብለዋል።
ዶክተር ተስፋዬ አክለውም ችግር ውስጥ ገብተዋል ያለቻቸውን የተመድ ሰራተኞች ማስወጣት የሚያግዳት ሕግ የለም ብለዋል።
ግለሰቦቹ በዓለም ዓቀፍ ስምምነት መሰረት የተሰጣቸውን የሃላፊነት ድንበር ጥሰው ከተገኙ አገራት እርምጃ መውሰድ ይችላሉ ብለዋል።
''አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ማስወጣት ብቻ ሳይሆን ቀድሞውኑ ወደ አገሬ እንዳይገቡ የማለት መብት ጭምር አላት'' በማለት የሁኔታውን ተገቢነት አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ሲያደርግ ግን ''እርዳታ አልፈልግም ወይም የእርዳታ ሂደቱን ማደናቀፍ ተደርጎ መወሰድ የለበትም'' ብለዋል።
እንደ ዶክተር ተስፋዬ ገለጻ በቀጣይ ከሁሉም በላይ በኢትዮጵያ በኩል የዲፕሎማሲያዊ ስራዎች ሊጠናክሩ ይገባል።
የኢትዮጵያ መንግስት ያስወጣቸው የተመድ ሰራተኞች ያልተገቡ ቁጥሮችን የሚጠቅሱ፤ ከአሻባሪ ቡድኑ ጋር በተለያየ መልኩ የሚገናኙ መሆናቸው ይታወሳል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በዚሁ ጉዳይ ለመንግስታቱ ድርጅት ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወቃል።
በማብራሪያቸውም አንድ አገር ወደ ግዛቷ ማን እንደሚገባ፤ እንደሚወጣና እንደሚቆይ የመወሰን መብቷ የተጠበቀ መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስትም ይህንን ውሳኔውን ለማንም ማሳወቅ አይጠበቅበትም ሲሉም ተናግረዋል።