ቀጥታ፡

"እየተፈጸሙ ያሉ ድርጊቶች የአገሪቱን መልካም ስም የሚያጎድፉ ናቸው"- ቤተ-ክርስቲያን

አዲስ አበባ  ነሀሴ 11/2010 በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እየተፈጸሙ ያሉ ድርጊቶች አገሪቱ በታሪክ፣ በባህልና በሃይማኖት ያላትን መልካም ስም የሚያጎድፍ መሆኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ገለጸች። በመሆኑም መንግስት የዜጎችን ደህንነት፣ የአገር ሰላምና አንድነትን ለመጠበቅም የህግ የበላይነትን እንዲያስከብር ቤተ-ክርስቲያኗ ጥሪ አቅርባለች። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ ወቅታዊ የአገሪቱ ሁኔታዎችን በማስመልከት መግለጫ ሰጥቷል። ፓትሪያርኩ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እንደገለጹት፤ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሰብአዊነት የጎደላቸውና የኢትዮጵያን መልካም ስም የሚያጎድፉ ተግባራት እየተፈጸሙ ይገኛሉ። በዚህም "ሃይማኖት የሌለው ሰው እንኳን የማይፈጽመው ድርጊት በሶማሌ፣ በባሌ፣ በሻሸመኔ፣ በጣና በለስና በሌሎችም አካባቢዎች ተፈጽመዋል" ብለዋል። በእነዚህ ግጭቶች ሳቢያ ለጊዜው የታወቁ ዘጠኝ አብያተ-ክርስቲያናት በንብረት ዝርፍያና በቃጠሎ መውደማቸውን፣ አምስት ካህናትም በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን፤ እንዲሁም ሰባት ካህናትና ሌሎችም ምዕመናን ላይ ድብደባ መፈጸሙን አውስተዋል። "ይህ ዘግናኝና አሳፋሪ ድርጊት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያንን ብቻ ሳይሆን መላ ኢትዮጵያዊያንን ያሸማቀቀ ድርጊት ነው" ያሉት  ፓትርያርኩ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ተጎጂዎችን ለመርዳት እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርበዋል። የፈረሱትንና የተቃጠሉትን አብያተ-ክርስቲያናት እንደገና እንዲቋቋሙ በሚደረገው ጥረትም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። የዜጎችን ደህንነት፤ ብሎም የአገርን ሰላምና አንድነት ለመጠበቅም መንግስት እርምጃዎችን እንዲወስድና የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራንና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ ወጣቶችና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በጽናት በመቆም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል። "ታላቅና ገናና የሆነች ኢትዮጵያ በአንድነቷ እንደተከበረችና ሃያል እንደሆነች እንድትቀጥል በተለይ ወጣቶችም በስሜታዊነት በወገን ላይ መጨከንን እንዲያቆሙና በማስተዋልና አርቆ አሳቢነት እንዲንቀሳቀሱም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም