ቀጥታ፡

ማህበሩ በአሸባሪው ቡድን የተጉዱ ከ200 ሺህ የሚበልጡ ወገኖችን ደገፈ

ጎንደር፤ መስከረም 27/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አሻባሪው የህወሃት ቡድን በአማራ ክልል በፈጸመው ወረራ ጉዳት ለደረሰባቸው ከ200 ሺህ ለሚበልጡ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ።
 ከማህበሩ ድጋፍ ውስጥ በሰሜን ጎንደር ዞን በጭናና በቦዛ ቀበሌዎች በወራሪው ቡድን ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው ከ1 ሺህ 200 በላይ አባወራዎች ሰሞኑን ያበረከታቸው ይገኙበታል።

የማህበሩ የኮሙዩኒክሽን ሃላፊ ዶክተር ሰለሞን ዓሊ ለኢዜአ እንደተናገሩት ፤ ማህበሩ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በማገዝ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት ጥረት እያደረገ ይገኛል።

እስካሁንም በተለይ በአማራ  ክልል በወረራው  ሳቢያ ቤት ንብረታቸው  ለተጎዳባቸው ከ200 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች ድጋፍ  ማድረጉን ገልጸዋል።

በዚህም ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁስ መሰጠቱን አስታውቀዋል።

ድጋፉንም ያደረገው ከአጋር ድርጅቶች፣  በውጭ ከሚኖሩ  ኢትዮጵያውያን፣  ከበጎ አድራጎት ማህበራትና ከህብረተሰቡ በማሰባሰብ መሆኑንም ዶክተር ሰለሞን አመላክተዋል።

ማህበሩ ለተጎዱ ወገኖች ፈጥኖ በመድረስ ማህበራዊ ሃላፊነቱ መወጣት እንዲችል ድጋፉ  እንዲቀጥል ሃላፊው ጠይቀዋል።

በክልሉ በደሴ፣ መቄት፣ ንፋስ መውጫና  እብናት አካባቢዎች ሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በማህበሩ የአማራ ክልል ቅርጫፍ ሃላፊ አቶ ሻምበል ዋለ ናቸው።

ሰሞኑን በሰሜን ጎንደር ዞን በዳባት ጭና ቀበሌ ቤት ንብረታቸው ለተጎዳባቸው 500 አባወራዎች እንዲሁም በደባርቅ ቦዛ ቀበሌ ለ700 አባወራዎች የቤት መገልገያ ቁሳቁስ፣  አልባሳትና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

''ወራሪው የሽብር ቡድን ከልብስ እስከ ቤት ዕቃ ድረስ አንድም ሳያስቀር ዘርፎ ወስዶብናል'' ያሉት በደባርቅ ወረዳ የቦዛ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሙሃባው አዲሱ ናቸው፡፡

ቡድኑ የቤት እንስሳቶቻችን በሙሉ አርዶ ከመብላቱም በላይ የጋማ ከብት ሳይቀር   መውሰዱንም ገልጸዋል።

ማህበሩን ችግሩን ለመቋቋም  ላደረገላቸው ድጋፍም  ምስጋና አቅርበው፤ መልሰው  መቋቋም እንዲችሉ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

የቦዛ ቀበሌ ነዋሪ  ተማሪ ባንቺ ጀማው በበኩሏ፤ ወራሪው የሽብር ቡድን የቤተሰቦቿን ንብረት፣ የቤት እንስሳትና እህል ዘርፎ በመውሰዱ ለችግር አጋልጦናል ብላለች።

አሁን ላይ እየተደረገ ያለው ዕለታዊ ድጋፍ ችግሩን በተወሰነ ለመቋቋም የሚያግዝ ቢሆንም በዘላቂነት ለመቋቋም  ተጨማሪ ድጋፍ ሊደረግልን ይገባል ስትል አመልክታለች።

ማህበሩ በቀጣይ የተፈናቀሉ ወገኖችን  መልሶ በማቋቋም  ሂደትም   ተሳትፎ  እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም