በኢትዮጵያ ፖለቲካ አመራርነትን ጠቅልሎ የሚያዝበት የአውራ ፓርቲ ስርዓት አብቅቶ በጋራ ወደ መምራት እየተሸጋገርን ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ፖለቲካ አመራርነትን ጠቅልሎ የሚያዝበት የአውራ ፓርቲ ስርዓት አብቅቶ በጋራ ወደ መምራት እየተሸጋገርን ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 27/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ፖለቲካ አመራርነትን ጠቅልሎ የሚያዝበት የአውራ ፓርቲ ስርዓት አብቅቶ አገርን በጋራ ወደ መምራት እየተሸጋገርን ነው ሲሉ የኢዜማ ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ ተናገሩ።
የኢዜማ ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት አዲሱ የፖለቲካ አደረጃጀት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ መንግስትና ፓርቲ መለያየታቸውን በተግባር ያሳየ ነው።
ቀደም ሲል የኢትዮጵያ የፖለቲካ "የአውራ ፓርቲ ስርዓት ነበር" ያሉት ዶክተር ጫኔ ገዥው ፓርቲ ስልጣንን ጠቅልሎ በመያዝ ሌሎችን የሩቅ ታዛቢ ያደርግ እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን መንግስት የሆነው ብልፅግና ፓርቲ ግን ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመስራት ያለው ፍላጎት እና በተግባርም ወደ ሃላፊነት ማምጣቱ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
በኩል የተቃውሞ ሃሳብ ያላቸው የሚታፈኑበት፣ የሚታሰሩበትና የሚሰደዱበት የሴራ ፖለቲካ አብቅቶ ከነሃሳብ ልዩነታቸው ወደ ሃላፊነት መምጣታቸው ሁሉንም ያስደሰተ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ አካታች የሆነ የዴሞክራሲ ስረዓት ለማምጣት ጥሩ መሰረት የሚጥልና ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሂደት መልካም ጅማሮ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቀጣይም በኢትዮጵያ ጠንካራ የፖለቲካ ውሳኔ የሚፈልጉ አጀንዳዎችን በጋራ ተቀራርቦ ለመወያየትና ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሚያስችል ምዕራፍ ከፍቷል ብለዋል ዶክተር ጫኔ።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ አመራርነትን ጠቅልሎ የሚያዝበት የአውራ ፓርቲ ስርዓት አብቅቶ አሁን ላይ አገርን በጋራ ወደ መምራት አዲስ ምእራፍ እየተሸጋገርን እንገኛለን ብለዋል።
አሁን ባለው የፖለቲካ አደረጃጀት ከህዝብ ጋር ተቀናጅቶ መስራት ከተቻለ ኢትዮጵያ የገጠሟትን ወቅታዊ ችገሮች መሻገር የሚያስችላት መሆኑንም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት መመሪያ መሰረት አዲስ ተሿሚ ሚኒስትሮች ጎጠኝነት የማይታይባቸው፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች አገልጋይ፣ ሌብነትን ለማጥፋት ቆርጠው የተነሱ መሆን አለባቸው ብለዋል።
ልመናን በማስቀረት በምግብ ራሷን የቻለች አገር በመገንባት ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብም መሰረት የሚጥሉ መሪዎች መሆን አለባቸው ነው ያሉት።
በእርዳታ ሰበብ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ጥያቄ ውስጥ በማስገባት እንዲሁም በእጅ አዙር ቅኝ ለመግዛት የሚጥሩ የውጭ ሃይሎችን ማስቆም የሚቻለው ከምንም በላይ በምግብ ራስን መቻል ሲኖርብን ነው ብለዋል።
ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የቀረቡ የ22 ሚኒስትሮች መሾማቸው ይታወቃል።
ከእነዚህ መካከል ሶስቱ ሚኒስትሮች ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ የተሾሙ አመራሮች ናቸው።