የተሾሙት ሚኒስትሮች ህዝብ እያስተባበሩ አገራዊ ችግሮችን ለመፍታት መስራት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የተሾሙት ሚኒስትሮች ህዝብ እያስተባበሩ አገራዊ ችግሮችን ለመፍታት መስራት አለባቸው

አዲስ አበባ፣መስከረም 27/2014 (ኢዜአ) አዲስ የተሾሙት ሚኒስትሮች ህዝብ እያስተባበሩ አገራዊ ችግሮችን ለመፍታት መስራት እንዳለባቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው 1ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የቀረቡ የ22 ሚኒስትሮችን ሹመት አጽድቋል።
ኢዜአ የሚኒስትሮች ሹመቱን በሚመለከት በመዲናዋ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት አዲስ የተሾሙት ካቢኔዎች ህዝብን እያስተባበሩ አገራዊ ችግሮችን ለመፍታት መስራት ይጠበቅባቸዋል።
ከመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ አወል አሊ፤ አዲስ ተሽሚዎች ያካበቱትን ልምድና ክሕሎት በመጠቀም አገራቸውንና ህዝባቸውን ከድህነት ለማስወጣት መስራት አለባቸው ብለዋል።
በመንግስት ሃላፊነት ላይ የተቀመጡ ሚኒስተሮች ህዝብን በማስተባበር ኢትዮጵያን ከችግር ማሻገር ይጠበቅባቸዋልም ነው ያሉት።
መንግስት ኢትዮጵያን ከድህነት ለማውጣት፣ ወደ ብልፅግና ለማሸጋገር እንዲሁም ውጫዊ ጫናዎችን በመቋቋም ወስጣዊ ችግሮችንም ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሚኒስትሮችን በስራ ልምዳቸው፣ በእውቀታቸው፣ በብቃትና ህዝብን የማገልግል ፍላጎታቸው መሰረት አድርገው መሾማቸው ተገቢ መስፈርት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ አቶ ማህቶት ጥላሁን ናቸው፡፡
በመሆኑም የሚኒስትሮቹ ሹመት ትክክለኛ መሆኑን ጠቅሰው በየደረጃው ያሉ የተቋማት ሃላፊዎችንም እየፈተሹ ማስተካከል ይገባል ብለዋል።
መንግስት በአገር ጉዳይ ሁሉንም በማሳተፍ ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር በማሳየቱ የሚደነቅ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ ኪሩቤል ታዬ ናቸው።
የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን ለይስሙላ ሳይሆን ተቋማትን እንዲመሩና ለውጥ እንዲያመጡ ሃላፊነት መስጠቱ በኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ ባህል እየተፈጠረ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።
አዲስ የተሾሙ ሚኒስትሮች ሌብነትና ልመናን የሚዋጉ፣ የብሄር ሳይሆን የመላ ኢትዮጵያ ህዝብ አገልጋይ ሆነው እንዲሰሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መመሪያ መስጠታቸው ተገቢ መሆኑንም አስተያየት ሰጭዎቹ ተናግረዋል።
የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችም አገር ለማሸገርና ተቋማትን በውጤታማነት ለመምራት ሃላፊነት ተቀብለው ለመስራት መዘጋጀታቸው መልካም ጅማሮ መሆኑን ገልጸዋል።
ከተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች መካከል የኢዜማ ፓርቲ መሪ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ - የትምህርት ሚኒስትር፣ የአብን ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላ - የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር፣ የኦግ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ቀጄላ መርዳሳ - የባህልና ስፖረት ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ይታወቃል።