የኢትዮጵያ መንግስት በግዛቱ ውስጥ ማን ንደሚገባ፤እንደሚወጣና እንደሚቆይ ለማንም ማሳወቅ አይጠበቅበትም - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መንግስት በግዛቱ ውስጥ ማን ንደሚገባ፤እንደሚወጣና እንደሚቆይ ለማንም ማሳወቅ አይጠበቅበትም
መስከረም 27/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንግስት በግዛቱ ውስጥ ማን እንደሚገባ፤እንደሚወጣ ለማንም ማሳወቅ አይጠበቅበትም ሲሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።
አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በኢትዮጵያ ከተልዕኳቸው ውጪ ሲንቀሳቀሱ ከአገር እንዲወጡ የነበሩ የተመድ ሰራተኞችን በተመለከተ ለጸጥታው ምክር ቤት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አምባሳደሩ በሰጡት ማብራርያ “የዛሬው ስብሰባ መነሻ ምክንያት የአንድን ሉዐላዊ ሀገር ውሳኔ የሚጋፋ የመወያያ አጀንዳ መፍጠሩ ተገቢ ካለመሆኑ በላይ ራስን በራስ በማስተዳደር በተወሰነ ውሳኔ ላይ እንዲሁም በሉዐላዊ አገር ጉዳይ ጣልቃ መግባት ነው” ብለዋል።በአለም አቀፍ ህጎች መነሻነት ኢትዮጵያ ውሳኔውን መወሰኗንም አስታውቀዋል።
የተለያዩ አገራት በተለያየ ጊዜ የተመድ ሰራተኞችንና ዲፕሎማቶችን ከተሰጣቸው ተልዕኮ ውጪ ተንቀሳቅሰዋል በማለት ያለ ምንም ማብራርያ ከአገር ማስወጣታቸውን አስታውሰው፤ ተመድ በእነሱ ላይ ጥያቄ አንስቶ ያውቃል ወይ ? ሲሉ ጠይቀዋል።
“የኢትዮጵያ መንግስትም ይህንን ውሳኔውን ለማንም ማሳወቅ አይጠበቅበትም” ሲሉ ገልጸዋል።አንድ ሀገር በግዛቷ ውስጥ ማን እንደሚገባ ፤እንደሚወጣና እንደሚቆይ የመወሰን መብቷ በተፈጥሮም ሆነ በአለም አቀፍ ህጎች የተጠበቀ ነው ያሉት አምባሳደር ታዬ የሰብአዊ ድጋፍ ከሚጠይቀው የስራ ስነ ምግባርና እንቅስቃሴ ውጪ የተሰማሩ የተመድ ሰራተኞች ላይ የተወሰደ እርምጃ ነው ሲሉ አመልክተዋል።
በየትኛውም ሁኔታ ሰብአዊ ድጋፍ ሰጪ አካላት በሰብአዊ ድጋፍ ስራ ብቻ መሰማራት እንዳለባቸው ህጎች መቀመጣቸውን አስታውሰው ኢትዮጵያም ከሰብአዊ ድጋፍ ስራ ውጪ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ እና ቀይ መስመርን ያለፉ አካላትን ከአገር እንዲወጡ አድርጋለች ብለዋል።
ዜጎች በርሃብ ሞተዋል በሚል ሃሰተኛ መረጃዎችን በማሳራጨት ለአሸባሪው ህወሃት በተለየየ መንገድ ድጋፍ በማደረጋቸው፣ በሰብአዊ ድጋፍ መስጫ ስፍራዎች የአሸባሪውን ቡድን አባላት በማስገባትና ለሽብር ቡድኑ የመገናኛና የህክምና መሳሪያ ድጋፍ በማድረጋቸው ከአገር እንዲወጡ መደረጉን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት እዚህ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት በተለያዩ ጊዜያት የተመድ ሰራተኞችን ከተሰጣተቸው ትልዕኮ ውጪ መንቀሳቀሳቸውን የሚያመለክቱ ደብራቤዎችን መጻፉን አረጋግጠው የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ለተመድ ማስታወቁን አመልክተዋል።
አሁንም ቢሆን ተመድ ለተልዕኮአቸው ብቁ የሆኑና በአንድ አገር የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ የማይገቡ የሰብአዊ ድጋፍ ሰራተኞችን በመላክ ድጋፉን እንዲቀጥል ጠይቀዋል።