አዲሱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አወቃቀር ከፖለቲካ አመለካከት በላይ አገርን ያስቀደመ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አወቃቀር ከፖለቲካ አመለካከት በላይ አገርን ያስቀደመ ነው
መስከረም 26 / 2014 (ኢዜአ) አዲሱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አወቃቀር ከፖለቲካ አመለካከት በላይ አገር መቅደም እንዳለበት በተግባር ያሳየ መሆኑን ተሿሚ ሚኒስትሮች ገለጹ።
ሚኒስትሮቹ ሌብነትን በመታገል ዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት የመንግስታቸውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት ሹመት አጸድቀዋል።
22 ሚኒስትሮችን የያዘው አዲሱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አደረጃጀት ከብልጽግና ፓርቲ ባለፈ ሶስት የተፎካካሪ ፓርቲ አመራር አባላትን አካትቷል።
ቀደም ባሉት ዓመታት በምርጫ ያሸነፈ ፓርቲ ከራሱ አባላት ውጭ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በስልጣን ማሳተፍ ያልተለመደ ተግባር ነበር።
ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ከምርጫው በፊት ፓርቲያቸው ካሸነፈ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በመንግስት ሃላፊነት ላይ በመሾም እንደሚያሳትፉ ቃል መግባታቸው አይዘነጋም።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተሿሚ ሚኒስትሮችም እንዲህ ዓይነት የሚኒስትሮች ምክር ቤት አደረጃጀት "የዴሞክራሲ ስርዓትን ለማሳደግ ከፖለቲካ ልዩነት ይልቅ አገር ማስቀደምን ያስተማረ ነው" ብለዋል።
ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የተሻለ አገር ለመገንባት አልመው የተመሰረቱ መሆናቸውን አመልክተው፤ በአገር ጉዳይ ላይ ተቀራርበው መስራታቸው ዓላማቸውን በቀላሉ ለማሳካት የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።
አዲሱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የፖለቲካ ልዩነቱን ወደ ኋላ ጥሎ አገርን ከችግር ለማውጣት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ሚኒስትሮቹ አረጋግጠዋል።
እንደ ሚኒስትሮቹ ገለጻ፤ አገርን በማልማት ወደ ብልጽግ ማሻገር የሚቻለው ከታችኛው የመንግስት አደረጃጀት ጀምሮ ግልጽ አሰራሮች በመፍጠርና ሌብነት ሲጠፋ ብቻ ነው።
ዜጎች ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዳይሆኑና በድህነት ውስጥ እንዲማቅቁ የሚያደርገውም "ሌብነት ነው" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ በአዲሱ የመንግስት መዋቅር የጣለውን እምነት በታማኝነት በቅንነት ለመፈጸም የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላቱ ያላቸውን ቁርጠኝነትን አረጋግጠዋል።
ለዚህ ደግሞ እያንዳንዱ ዜጋ ሌብነትን በማጋለጥ በመከላከል ድጋፍ እንዲያደረግ ጠይቀዋል።