ቀጥታ፡

አዲሱን የአስፈፃሚ አካላት ሹመት አስመልክቶ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የሰጡት ሽፋን

መስከረም 26/2014 (ኢዜአ) የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን አዲሱ መንግስት የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ዎችን ያካተተ የሚኒስትሮችን ሹመት ማድረጉን ዘግበዋል።

አዲሱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ጉባኤ የሚኒስትሮችን ሹመት አጽድቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ካቢኔያቸውን ይፋ ሲያደርጉ ሶስት የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን በሃላፊነት ሾመዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላ እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ቀጄላ መርዳሳ በሚኒስትርነት ተሾመዋል።

ይህንን የአስፈፃሚ አካላት ሹመት በተመለከተ በርካታ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን ሰጥተውታል።

ከሚዲያዎቹ መካከል ሮይተርስ፣ አልጀዚራ፣ ዘ- ስታር፣ ኤ ኤፍ ፒ፣ ብሉምበርግ፣ ዘ ጋርዲያን የመሳሰሉት ሽፋን ከሰጡ መካከል ይጠቀሳሉ።

መገናኛ ብዙሃኑ በምክር ቤቱ ሹመታቸው ከጸደቀላቸው 22 ሚኒስትሮች መካከል ሶስቱ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ውስጥ መሆናቸውን በዘገባቸው አመልክተዋል።

ሶስቱ ከተፎካካሪ ፓርቲ የተሾሙት ሚኒስትሮች መንግስት አካታችነትን ለማረጋገጥ የገባውን ቃል ማሳያ እንደሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃን በማጣቀስ ዘግበዋል።

መገናኛ ብዙሃኑ በአዲሱ የካቢኔ አወቃቀር የአመራር ሽግሽግ መደረጉንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም