ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለመዲናዋ ነዋሪዎች ምስጋና አቀረቡ

መስከረም 26 / 2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሰሞኑን በመዲናዋ የተከናወኑ ትላልቅ አገራዊ መርኃ ግብሮች በተሳካ መልኩ እንዲጠናቀቁ ሕዝቡ ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋና አቀረቡ።

ከንቲባዋ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ በአዲስ አበባ የተከናወኑ የመስቀል ደመራ በዓል፣ ኢሬቻና የአዲስ መንግሥት ምሥረታ በተሳካ መልኩ ተጠናቋል።

ለዚህ ደግሞ የአዲስ አበባ ሕዝብ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበሩና መርኃ ግብሮቹ እንዳይስተጓጎሉ በራስ ተነሳሽነት ያበረከታቸውን ሌሎች አስተዋጽኦዎች ጠቅሰዋል።

በተለይም የመስቀል ደመራ በዓል በመስቀል አደባባይ ብቻ ሳይሆን በመዲናዋ ከሁለት ሺህ በላይ በሆኑ የተለያዩ ሥፍራዎች ላይ መከበሩን ጠቁመው፤ ያለምንም ችግር መጠናቀቁን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የኢሬቻና አዲሱ የመንግሥት ምሥረታ በደማቅ ሁኔታ የአገሪቷን ገፅታ በሚያሳይ እንዲሁም ኢትዮጵያዊ እሴቶችን በሚያጠናክር መልኩ መጠናቀቃቸውን ነው የገለጹት።

ለዚህም የከተማዋ ሕዝብ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በመንገድ መዘጋት ህዝቡ መንገላታት ሳይሰማው በተለያየ መንገድ ተደጋጋሚ ፍተሻዎች ሲደረጉ ተባባሪ እንደነበር ገልጸው፤ ለጸጥታ አካላት መረጃ በመስጠት ጭምር ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበር አንስተዋል።

"በታሪካችን ውስጥ አዲስ ታሪክ በመጻፍ በኩል ትልቅ ድርሻ ተጫውቷል እና በድጋሚ የአዲስ አበባን ወጣቶች ጸጥታ በማስከበር ስነ ሥርዓት በማስያዝም ትልቅ ድርሻ ሲጫወቱ የነበሩትን የአዲስ አበባ ሕዝብ በጥቅሉ እጅግ አድርጌ ላመሰግን እወዳለሁ" ብለዋል ከንቲባዋ።

ሕዝቡ የከተማዋን አስተዳደር ጨምሮ በአዲሱ መንግሥትትልቅ ተስፋ እንዳለው ጠቅሰው፤ ይህንን ሕዝብ በታማኝነትና በትጋት ለማገልገል በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

"የአዲስ አበባ ሕዝብ ትልቅ ሃላፊነት ጥሎብናል፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳደረገው ሁሉ በተለየ ሁኔታ ደግሞ ትልቅ ሃላፊነትን የተወጣ ሕዝብ ከመሆኑ አንጻር በተለየ ሁኔታ አቅደን በተገቢው አክብሮት ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት ዝቅ ብለን በማገልገል ይሄን ሕዝብ መካስ እንደሚገባን ጭምር ሃላፊነት የወሰድንበት ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም