በአብዛኛው በደቡብና በምዕራብ አጋማሽ የአገሪቱ ክፍሎች በመጪዎቹ አምስት ቀናት የተሻለ ዝናብ ይጠበቃል - ኢዜአ አማርኛ
በአብዛኛው በደቡብና በምዕራብ አጋማሽ የአገሪቱ ክፍሎች በመጪዎቹ አምስት ቀናት የተሻለ ዝናብ ይጠበቃል

መስከረም 26/2014 (ኢዜአ) በአብዛኛው በደቡብና በምዕራብ አጋማሽ የአገሪቱ ክፍሎች በመጪዎቹ አምስት ቀናት የተሻለ ዝናብ የሚጠበቅ መሆኑን የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ።
ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው የክረምቱ ዝናብ በምዕራብ አጋማሽ የሚቀጥል ይሆናል።
በተጨማሪም የዝናብ ስርጭቱ ወደ ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ ሊስፋፋ እንደሚችል ይቁማል።
ከኦሮሚያ ጅማ፣ ኢሉአባቦር፣ ሁሉም የወለጋ ዞኖች፣ አርሲና ባሌ፣ ምዕራብ ሐረርጌ፣ የጉጂ ዞኖች፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ በሚቀጥሉት አምስት ቀናት በአብዛኛው ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ እንደሚያገኙ ይጠበቃል።
ከአማራ ክልል የሰሜንና የደቡብ ጎንደር ዞኖች፣ ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም፣ ሰሜን ሸዋ እንዲሁም የባህርዳር ዙሪያ እና አገው አዊ ተመሳሳይ የዝናብ መጠን ይኖራቸዋል ተብሎ ይገመታል።
ከደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ደቡብ ኦሞ በስተቀር በሁሉም ዞኖች እንዲሁም በሲዳማ ክልል ዞኖች በአብዛኛው ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ እንደሚያገኙም ተጠቁሟል።
በሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ በአፋር ክልል ዞን 3 እና 5፣ ምስራቅ ሐረርጌ፣ ድረደዋና ሐረሪ፣ ከሶማሌ ክልል የሰሜን፣ የመካከለኛ የደቡብ ምስራቅ ዞኖች፣ በአዲስ አበባ አና ጋምቤላ አነስተኛ ዝናብ ይጠበቃል።
የተቀሩት የአገሪቱ ክፍሎች ደረቅ ሆነው እንደሚቆዩ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ መረጃ አመልክቷል።
የመኽር ሰብል አምራች በሆኑትም ሆነ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች የእርጥበት ሁኔታው ከቀደመው አንጻር ሲታይ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ጥንካሬ ይዞ ሊቀጥል እንደሚችል ይጠበቃል።
በምዕራባዊ አጋማሽ የደቡብና ደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ የአገሪቱ ክፍሎች ያለው ዝናብ ለግብርና ስራ እንቅስቃሴ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሏል።
ዘግይተው ለተዘሩትና እድገታቸውን ላልጨረሱት እንዲሁም በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ ለሚገኘው የመኽር ሰብሎችና ለቋሚ ተክሎች የውሃ ፍላጎት ያሟላል ተብሎ ይጠበቃል።
በአብዛኛው ባሮአኮቦ፣ ኦሞጊቤና ስምጥ ሸሎቆ፣ የደቡባዊና የምዕራባዊ አጋማሽ አባይ፣ የላይኛው አዋሽ፣ የላይኛውና መካከለኛ ዋቢ ሸበሌና በአብዛኛው የገናሌዳዋ ተፋሰሶች እርጥበት እንደሚያገኙ ይጠበቃል።
በአብዛኛው አዋሽ፣ ምስራቃዊ አባይ፣ የታችኛው የገናሌዳዋ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ የታችኛው ባሮአኮቦ አና የላይኛውና የመካከለኛው ዋቢ ሸባሌ ተፋሰሶች መጠነኛ እርጥበት መጠን እንደሚያገኙ ይጠበቃል።
በአብዛኛው የበጋ ወቅት እንደሚስተዋለው የሰሜን አጋማሽ የኢትዮጵያ ክፍሎች ላይ የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማ እና ነፋሻማ የአየር ጠባይ ጎልቶ ከመታየቱ አንጻር የሌሊቱ የማለዳው ቅዝቃዜ መጨመር ያሳያል ሲል የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ በመግለጫው አመልክቷል።