ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ጉዳይ ተለያይተን ከቆምን ጠላት እናፈራለን እንጂ የትም አንደርስም

አዲስ አበባ፣ መስከረም 25/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ጉዳይ ተለያይተን ከቆምን ጠላት እናፈራለን እንጂ የትም ስለማንደርስ ከልዩነት ይልቅ አንድነታችንን ልናጠናክር ይገባል ሲሉ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የኢዜአ ሪፖርተር ከአዲሱ መንግስት ምስረታና የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዓለ ሲመትን በማስመልከት በአዲስ አበባ ተዘዋውሮ ነዋሪዎችን አነጋግሯል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የታደሙት የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና የኢትዮጵያ ሕዝብ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

"ኢትዮጵያ እናታችን፣ የአፍሪካዊያን እናት፣ በቅኝ ያልተገዛች የነፃነት ተምሳሌት" እንዲሁም ሌሎች ሃሳቦችን በማካተት መሪዎቹ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። 

የመሪዎቹ ንግግር ትልቅ መልእክት ያዘለ መሆኑን የሚናገሩት የመዲናዋ ነዋሪዎች ኢትዮጵያዊያን ምክራቸውን ልንቀበል፤ መልእክታቸውንም በደንብ ልናጤነው ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ጉዳይ ተለያይተን ከቆምን ጠላት እናፈራለን እንጂ የትም ስለማንደርስ ከልዩነት ይልቅ አንድነታችንን ልናጠናክር ይገባል ነው ያሉት አስተያየት ሰጭዎቹ።

ከመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሳረው ዘዮንስ፤ ሌሎች አገሮች በኢትዮጵያ ሲመኩ፤ የአፍሪካ ኩራት መሆኗን ደጋግመው ሲነግሩን በድንብ ልናደምጣቸውና ለአገራችን በጋራ ልንቆም ይገባል ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት የኢትዮጵያን ህዝብ ለመከፋፈልና አንድነታችንን ለመሸርሸር የተከለውን ጥላቻ ነቅለን ማድረቅ አለብንም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ያስከበረች ትልቅ አገር በመሆኗ አገራችንን እንደተከበረች ለትውልድ ማስተላለፍ አለበን ብሏል ሌላኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ ወጣት ሄኖክ እንዳወቅ።

ሌሎች እያከበሯት ያለችውን አገራችንን እኛም በጋራ ሆነን አክብረን ልናስከብራት፣ ልንኮራባትም ይገባል ብሏል።

ለአገራችን ስንል ሁላችንም በፍቅር በመስራት የተጋረጡብንንም ፈተናዎች በጋራ ማሸነፍ አለብን ብለዋል አስተያየት ሰጭዎቹ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ዶክተር አቢይ አህመድን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ የሰየመ ሲሆን  በዓለ ሲመታቸውም የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ተከናውኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም