መንግስት የኢትዮጵያን አንድነት በማጠናከር ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን መፍታት አለበት - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የኢትዮጵያን አንድነት በማጠናከር ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን መፍታት አለበት
አዲስ አበባ፣ መስከረም 25/2014 (ኢዜአ) መንግስት የኢትዮጵያን አንድነት በማጠናከር፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን መፍታት የሚያስችሉ ስራዎች ላይ ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ "ኢትዮጵያንና መንግስቷን ባርክ፣ ጠብቅ" በማለት የጸሎት መርሀ ግብር አካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙ የሃይማኖት አባቶች ለኢዜአ በሰጡት አስተያያት አዲሱ መንግስትም ሆነ አጠቃላይ ህዝቡ ኢትዮጵያን ከተደቀኑባት ፈተናዎች መታደግ ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የፓትሪያርኩ ልዩ ጽህፈት ቤትና የውጭ ጉዳይ የበላይ ኃላፊ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ፤ የተመሰረተው መንግስት የሰላምና ፀጥታ ችገሮችን መፍታት እንዲሁም ለኑሮ ውድነት መፍትሄ መሻት አለበት ብለዋል።
ለወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀው መንግስት ብቻውን መወጣት ስለማይችል ህዝቡም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ መንግስትን በመደገፍ የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ ገልፀው የሃይማኖት ተቋማትም ለአገራቸው የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጸሀፊ ሼህ ቃሲም መሀመድ ታጁዲን፤ የተመሰረተው መንግስት በህዝብ ይሁንታ አግኝቶ ተመርጦ የመጣ በመሆኑ የህዝቡን ጥያቄ መመለሰ አለበት ብለዋል።
በተለይም የሰላም ጉዳይ ላይ፣ የኑሮ ውድነት እና የህግ የበላይነትን ከማስከበር አንፃር የቅድሚያ ስራው ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የሃይማኖት ተቋማት ደግሞ ትውልዱን በመግራት እና በማነጽ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ እየሱስ ሱራፌል አዲሱ መንግስት የሀገር አንድነትን በማስጠበቅ እና የኑሮ ውድነትን ከማሻሻል አንፃር ብዙ ይጠበቅበታል ይላሉ።
የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነቱ እንዲፀና ከማድረግ አንፃር መንግስት ያለበትን ሃላፊነት ሊወጣ ይገባዋልም ብለዋል።
በኢትዮጵያ መጭው ጊዜ የሰላም የአንድነት፣ የልማትና የብሩህ ተሰፋ እንዲሆን የሃይማኖት አባቶቹ ፀሎታቸውን አድርሰዋል፣ ለመላ ኢትዮጵያዊያን መልካም ምኞታቸውንም ገልጸዋል።