ቀጥታ፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓለ ሲመት የአፍሪካ አገራት መሪዎች ስለ ኢትዮጵያ ታላቅነት፣ የመሰከሩበት ታሪካዊ እለት ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 25/2014  (ኢዜአ) በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአለ ሲመት ላይ የተገኙ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ስለ ኢትዮጵያ  ታላቅነት፣ የአፍሪካ መሪነት፣ የነጻነት እናትነት በአደባባይ በጋራ የመሰከሩበት ታሪካዊ እለት መሆኑን ምሁራን ተናገሩ፡፡

በትላንትናው እለት በኢትዮጵያ አዲስ የመንግስት ምስረታ የተካሄደ ሲሆን በቀጣይ 5 አመታት ሀገሪቷን የሚመራው የብልጽግና ፓርቲ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሀገሪቷን መሪ አሰይሟል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን የአፍሪካ አገራት መሪዎች ስለ ኢትዮጵያ ያስተላለፉት መልእክት ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

አዲስ የተመሰረተው መንግስት የተጠራቀሙ አገራዊ ችግሮችን የተረከበና ድርብርብ ሃላፊነቶች ያሉበት መሆኑንም ተናግረዋል።

በባህር ዳር ዩንቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና የስነ-ተግባቦት መምህር ዶክተር ሙሉቀን አሰግደው፣ ሀገሪቷ በበርካታ ውጣ ውረድ ውስጥ ሆና አዲስ መንግስት መመስረቷን አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበዓለ ሲመታቸው ባደረጉት ንግግር ''ኢትዮጵያ ካዘመመችበት ቀና የምትልበት ጊዜው አሁን ነው'' ማለታቸው ኢትዮጵያን ለማሻገር ቆርጠው መነሳታቸውን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስተሩ በንግግራቸው ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ከፍታ ለመውሰድ ያነሱት ሃሳብም የህዝቡን ችግር መሰረት ያደረገ መሆኑን ዶክተር ሙሉቀን ጠቁመዋል።  

በአሁኑ ወቅት በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል በአሸባሪው ህወሃት ንጹሃን ላይ ያተኮረ የሽብር ተግባር እየተፈጸመ መሆኑን አንስተዋል።

ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ ለመስጠት መንግስት የአንበሳውን ድርሻ ሊወሰድና ህዝቡም ሊያግዘው ይገባል ብለዋል።

በአፋጣኝ ሊመለሱ ከሚገቡ የህዝብ ጥያቄዎች ጎን ለጎን የቆዩና ለለውጡም መነሻ የሆኑ እየተንከባለሉ የመጡ በርካታ ችግሮች እንዳሉም አንስተዋል፡፡

በመሆኑም የህገ መንግስት ማሻሻያ ለውጥና ሌሎች የቆዩ የህዝብ ጥያቄዎችን አዲሱ መንግስት በሂደት ምላሽ ሊሰጥባቸው ይገባል ብለዋል ዶክተር ሙሉቀን።

ኢትዮጵያ አሁን እየገጠሟት ያሉ የውጭ ጫናዎችን ለመቋቋም እያደረገች ያለችው ጥረት የሚበረታታ መሆኑንም አንስተዋል።

ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላት ትብብር በይበልጥ እየተጠናከረ መምጣቱ እና በርካቶቹ የኢትዮጵያ አጋር መሆናቸውን በተግባር ማሳየታቸው ጥሩ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በዓለ ሲመት ላይ የታደሙ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ስለ ኢትዮጵያ ያስተላለፉት መልእክትም ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።

መሪዎቹ  አንድ አገር ወዳድ ዜጋ ሊጠቀምበት የሚችለውን ቃል ተጠቅመው ኢትዮጵያን የገለፁበት መንገድ ለብዙዎቻችን አስደንቋል ብለዋል ዶክተር ሙሉቀን።

የኢትዮጵያን ታላቅነት፣ የአፍሪካ መሪነት፣ የነጻነት እናትነት በአደባባይ በጋራ የመሰከሩበት ታሪካዊ እለት መሆኑንም ገልፀዋል።

በዲላ ዩንቨርሲቲ የጋዜጠኝበትና የስነ-ተግባቦት መምህር አስናቀ እንድሪያስ፣ አዲሱ መንግስት ሁለንተናዊ ለውጦችን ለማምጣት ቃል መግባቱን ተናግረዋል።

መንግስት በተለይም ለስራ አጥነትና የኑሮ ውድነት ችግሮች አፋጣኝ መፍትሄ ማምጣት ይጠበቅበታል ያሉት ምሁሩ ለዚህም ህዝቡ ከመንግስት ጎን ሊቆም ይገባል ብለዋል።

ከውስጥና ከውጭ ያሉ ጫናዎችና የሰላም መደፍረሶችን  ለማስተካከል መንግስት ሁሉንም በማሳተፍ መንቀሳቀስ እንዳለበትም ጠቁመዋል።

በሽብር ተግባር ላይ በተሰማሩት ህወሃት እና ሸኔ ላይ ጠንካራ እርምጃ በመውሰድ በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም ማምጣት የመንግስት ዋነኛ የቤት ስራ ሊሆን ይገባዋል ብለዋል።

የአፍሪካ አገራት መሪዎች ኢትዮጵያን የገለጹበት መንገድ ሁላችንንም ያነቃ ጠንካራ መልእክት ነው ያሉት መምህር አስናቀ ሁላችንም ለአገራችን ህልውና በጋራ መቆም አለብን ሲሉ ተናግረዋል።

"ኢትዮጵያ በአፍሪካዊያን ዘንድ ያላት ምስል ትልቅ ነው" በማለት የዩጋንዳው ፕሬዝደንት ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ መልዕክት አስተላልፈዋል ነው ያሉት።

ዩጋንዳ ያሳለፈችው የመከፋፈል የፖለቲካ ስርዓት እሳቸው ባሳለፉት የ60 አመታት የአፍሪካ ፖለቲካ  ትግል ምን እንደነበር ያሰየ በመሆኑ ኢትዮጵያ ከዚህ ትልቅ ትምህርት ልትወስድ ይገባል ብለዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም