ቀጥታ፡

ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ጠንካራ ግንኙነት ይኖረናል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 25/2014 (ኢዜአ) "ከአዲሱ የኢትዮጵያ መንግስት ጋር  ጠንካራ  ግንኙነት ይኖረናል" ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊዎች ገለጹ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ሃላፊዎች፤ የመንግስት መስረታ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ለሚኖራት ግንኙነት አዲስ ምእራፍ የሚከፍት መሆኑን ገልጸዋል።

የጅቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር መሃመድ አሊ የሱፍ፤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት በቁርጠኝነት የሰራች አገር መሆኗን አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እያለፈች መሆኑን ጠቅሰው ሆኖም "ኢትዮጵያውያን ችግራቸውን በራሳቸው አቅም መፍታት የሚችሉ ጠንካራ ህዝቦች መሆናቸውን ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል" ብለዋል።

ጀቡቲ ሁሌም ከኢትዮጵያውያን ጎን የምትቆም ጠንካራ አቋም ያላት አገር መሆኗንም ነው ያብራሩት።

የጅቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኡመር ጊሌ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በዓለ ሲመት በመገኘት ያስተላለፉት መልዕክትም የኢትዮጵያና ጅቡቲን የማይናወጥ ወዳጅነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል።

ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ወዳጅነት ከሌሎች ሀገራት ጋር ካላት ግንኙነት ይለያል የሚሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ሁለቱ ሀገሮች በመሰረተ ልማት ጭምር የተሳሰረ ጥብቅ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የጅቡቲ መሰረተ ልማቶች በኢትዮጵያ ገበያን ለማሳለጥ እንደሚውሉ ሁሉ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ለጅቡቲ ሞተር ሆኖ  ያገለግላል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የተመሰረተው አዲስ መንግስት የሁለቱ አገራት ግንኙነትን ወደ አዲስ አድማስ እንደሚያሸጋግረው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።    

የኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ ጆን ሙሊምባ፤ ኡጋንዳና ኢትዮጵያ  በምንም አይንት ሁኔታ የማይቀየር አጋርነት እንዳላቸው ጠቁመዋል።

ሁለቱ አገሮች የአፍሪካ ቀንድን ወደ አንድ ለማምጣትና በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በጋራ እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ይህንኑ ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አውስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ኢትዮጵያን ለመምራት ድጋሚ እድል ስለተሰጣቸው መደሰታቸውንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ በሆነ አዲስ መንግስት መመስረታቸው የሚደነቅ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ ናቸው።

እስራኤል በዴሞክራሲ በጽኑ የምታምን ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ በዴሞክራሲያዊ ሂደት መንግስት ማቋቋሟ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በጎ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በቀጣይ ቀናት ካቤኔያቸውን ለምክር ቤቱ አቅርበው ያስጸድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም