ቀጥታ፡

የወከለንን ህዝብ ሃላፊነት ለመወጣት ተዘጋጅተናል

አዲስ አበባ መሰከረም 25/2014 የወከለንን ህዝብ ሃላፊነት ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉ የምክር ቤት አባላት ተናገሩ።

የፌዴሬሽንና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስድስተኛው ዙር የምስረታና የመክፈቻ ጉባኤ ተካሂዷል።

በምስረታው እለት ኢዜአ ያነጋገራቸው የሁለቱ ምክር ቤት አባላት ዜጎች በየጊዜው የሚያነሷቸው የመልካም አስተዳደርና የፍትህ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኙ በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ለወከልነው ህዝብ በሚመጥን መልኩ ሃላፊነታችንን በአግባቡ ለመወጣት ተዘጋጅተናልም ነው ያሉት። 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ አለም ዳምጠው እንዳሉት የመልካም አስተዳደር የሰላም የኑሮ ውድነት ችግሮች ላይ ውይይት በማድረግና መሻሻል ያለባቸው አሰራሮች ህጎች ተሻሽለው ህብረተሰቡ ከዚህ ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ መፍጠር መቻል አለብን ብለዋል።

''ማህበሰረቡ በኛ ትልቅ አደራ ጥሏል ተስፋም አለው በእርግጠኝነት ይሄን አደራውንና ተስፋውን እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት እንሰራለን'' ያሉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ወይዘሮ እታለ ፍትሃወቅ ናቸው።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል ዶክተር ባዩሽ ተስፋዬ በበኩላቸው ''በእኩልነት ሁሉን በማየት የወከለኝን ህብረተሰብ ለማገልግልና በመሰረተ ልማትም ይሁን በመልካም አስተዳደር ያሉበትን ችግሮች እፈታለሁ'' ብለዋል። 

''ውክልና ብቻ ሳይሆን ህዝባችን ጋር ወርደን የሚታዩ ችግሮችን የምንፈታበት እየተወያየን የሚነሱ ጉዳዮች ላይ በመተማመን በሀሳብ ልዕልና ስህተቶችን አርመን እየካስን ወደ ከፍታ ማማ ኢትዮጵያን እናደርሳለን።'' ያሉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል አቶ ዘነባ ሳጎያ ናቸው።

የኢትዮጵያ የሰላምና ጸጥታ ችግሮች፣ የኑሮ ውድነት እንዲሁም የውጭ አገራት ጫናዎችን መቋቋምና መመከት የሁላችንም ድርሻ ይሆናል ብለዋል የምክር ቤቱ አባላት።

በተለያዩ ምክንያቶች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች አፋጣኝ ድጋፍ እንዲያገኙና በዘለቄታው እንዲቋቋሙ ለማስቻልም በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።

በትናንትናው እለት በተካሄደው የመንግሰት ምስረታና የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በዓለ ሲመት የበርካታ አገራት መሪዎችና ዲፕሎማቶች እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች በታደሙበት በድምቀት መከናወኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም