የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጨማሪ ዓመታዊ የሀጂ ጉዞ ማቅረቡን ገለጸ

19
አዲስ አበባ ነሀሴ 11/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ በእስልምና እምነት እጅግ የተከበረውን ዓመታዊ የሀጂ ጉዞ ተጨማሪ በረራ ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡ አየር መንገዱ  ተጨማሪ በረራ ያዘጋጀው የሀጂ ጉዞ አስተባባሪ ኮሚቴ  ሰሞኑን በሱማሌ ክልል በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት ከጉዞ ዘግይተው የመጡ ሀጆች እንዲስተናገዱ በጠየቀው መሰረት ነው፡፡ እንዲሁም በሳዑዲ የአየር መንገድ በተያዘላቸው የበረራ ምዝገባ መሰረት ሊስተናገዱ ባለመቻላቸው ኮሚቴው  ተጨማሪ በረራ ጠይቋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ምንም እንኳን ወቅቱ ከፍተኛ የበረራ እንቅስቃሴ ያለበት ቢሆንም ብሔራዊ ግዴታውን በማክበር ለሙስሊሙ ማህበረሰብ አገልግሎቱን ማቅረቡ ተጠቅሷል፡፡ በተጨማሪም ነሐሴ 8 ቀን 2010ዓ.ም በነበረው መጥፎ አየር ጠባይ እና ከባድ ዝናብ ሳቢያ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪ ጣቢያ ብልሽት አጋጥሞት ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በወቅቱ የነበሩ ገቢም ሆነ ወጪ በረራዎችን ማስተናገድ ስላልተቻለ አዲስ አበባ ማረፍ የነበረባቸው ስድስት በረራዎች ጂቡቲ ለማረፍ ተገደው ነበር፡፡ በመሆኑም በዘገዩ በረራዎች ምክንያት ዘግይተው የደረሱ የሀጅ መንገደኞቻችንን ወደ ሆቴል መውሰድ ባለመቻሉም አየር መንገዱ ይቅርታ ጠይቋል፡፡ ተጨማሪ ለሚደረገው በረራም ከሳዑዲ ሲቪል አቪዬሽን የበረራ ፈቃድ በመጠባበቅ ሂደት በመንገደኞች ማስተናገጃ በረራውን ለሚጠብቁ ሀጆች የምግብና መሰል መስተንግዶዎች ማቅረቡም ተጠቁሟል፡፡ አየር መንገዱ ተጨማሪ አውሮፕላን በመመደብ ሁሉንም የሃጂ ተጓዦች ወደ ጉዞ መዳረሻቸው ማድረሱንም  ከኢትዮጵያ አየር መንድ ያገኘነው መግለጫ ያመለክታል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም