ግብጽ ወደ ቀልቧ መመለስ ልትጀምር ይሆን? - ኢዜአ አማርኛ
ግብጽ ወደ ቀልቧ መመለስ ልትጀምር ይሆን?
በሚዲያ ሞኒተሪንግና ትንተና
የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት በተለይም ግብጽ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የውኃ እጥረት እንደሚገጥማት ብዙ ስትወተውት መስማቱ የተለመደ ነው። ሆኖም ችግሩ የግብጻውያን የውኃ አጠቃቀም ከፍተኛ ብክነት የሚስተዋልበት በመሆኑ እንጂ የውሃ እጥረት እንደሌለባት የዘርፉ ምሁራን በተደጋጋሚ ይገልጻሉ። ከሰሞኑ የግብጹ ፕሬዝዳንት አል ሲሲ በውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ለህዝባቸው ያስተላለፉት ማስጠንቀቀያ አዘል መልእክት የምሁራኑን ሃሳብ ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ ነው።
ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ለግብጽ ህዝብ ባስተላለፉት መልእክት የውሃ አጠቃቀማቸው ማሻሻል እንዳለባቸው ጠንከር ያለ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። ባለፉት አስርት ዓመታት በመንግስት የተያዘ መሬትና የመስኖ ውኃን ከህግ ውጭ በያዙ ግብፃውያን ላይ የኃይል እርምጃ እንደሚወስዱም ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል። “ድርጊቱን መንግሥት ፈጽሞ ሊታገሰው የማይችል ነው” ሲሉ ያስጠነቀቁት ፕሬዝዳንት አል ሲሲ የውኃ አጠቃቀምን ለማሻሻል ግብጽ ከግዜ ጋር እየተሽቀዳደመች መሆኗን በመጥቀስ ይህን ለማስፈጸም ደግሞ ፖሊስና የጦር ኃይላቸውን ሊያሰማሩ እንደሚቸሉ አስጠንቅቀዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መካሄድ ከጀመረ ወዲህ በኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መካከል ላለፉት አስርት ዓመታት የዘለቀ ድርድር ሲደረግ ቆይቷል። ኢትዮጵያ ግድቡን የምትገነባው ልማቷን ለማሳለጥ እንደሆነ ብትገልጽም ግብጽና ሱዳን ጉዳዩን በቀላሉ የተመለከቱት አልሆነም። የህዳሴው ግድብ ግንባታ ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ይልቅ ፖለቲካዊ እንድምታ እንዲላበስ ለማድረግም ሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ። በተለይ ግብጽ።
የህዳሴ ግድቡ ለአካባቢው ሀገራት የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን ኢትዮጵያ በመረጃ አስደግፋ ግልጽ ስታደርግ ቆይታለች። በዚህ ረገድ አብዛኞቹ የላይኛው ተፋሰስ አገራት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን በአዎንታ ሲቀበሉት ግብጽና ሱዳን ግን እንዴት ተደርጎ ባይ ሆነዋል።
“እኛ ሳንፈቅድ እንዴት ይገነባል” ከማለት አንስቶ ግንባታው ፖለቲካዊ ገጽታ በመስጠት እስከ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አድርሰውታል። የውሃ ጉዳይ የልማት እንጂ የሰላምና ጸጥታ አጀንዳ ባለመሆኑ የጸጥታው ምክር ቤት ስለህዳሴው ግድብ መነጋገር አይጠበቅበትም ነበር። ይሁንና በግብጽ ግፊት ምክር ቤቱ ስብሰባ ሊቀመጥ ችሏል። ስለጉዳዩ ለጸጥታው ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ ለመስጠት ወደ ኒውዮርክ ያቀኑት የኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ስለሺ በቀለ “በጸጥታው ምክር ቤት የቀረብኩ የመጀመሪያው የውሃ ሚኒስትር ሳልሆን አልቀርም” በማለት የጸጥታው ምክር ቤት ለልማት በሚገነባ ግድብ ላይ በመወያየት ጊዜውን ባያባክን ሲሉ ምክር ቤቱን ወረፍ ማደረጋቸው የሚታወስ ነው። በወቅቱ የፀጥታው ምክር ቤትም የዶክተር ስለሺን ምክረ-ሃሳብ በተቀበለ መልሉ ጉዳዩን በአፍሪካ ህብረት በኩል እንዲታይ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል። ይህም ለኢትዮጵያ አንድ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ተደርጎ ተወስዷል።
የውሃ ምህንድስና ባለሙያ እና በህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው ግብጽም ሆነች ሱዳን ከህዳሴ ግድብ የሚያገኙትን ጥቅም ጠንቅቀው ያውቁታል ይላሉ። ለዚህ ደግሞ በጥናት የተደገፈ ማረጋገጫ እንዳላቸው ይናገራሉ። ይህን እያወቁ ግን የግድቡ ጉዳይ ፖለቲካዊ ገጽታ በማላበስ ኢትዮጵያ ከውሃ ሃብቷ እንዳትጠቀም ተጽዕኖ ለመፍጠር መሞከራቸው ተገቢ አይደለም ይላሉ።
ኢትዮጵያን ጨምሮ የላይኛው የናይል ተፋሰስ አገራት የቅኝ ግዛት ስምምነትን በፍትሃዊ አጠቃቀም በመተካት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ዲፕሎማሲያዊ መልክ እንዲኖረው እየሰሩ መሆናቸውን ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ ያስረዳሉ። ኢትዮጵያ ውሃውን በዕውቀትና በክህሎት ላይ ተመስርታ ለምትፈልገው የልማት ጥቅም የማዋሏን ተገቢነት ያነሳሉ።
ግብጽ “የውሃ ድርሻዬን ይቀንስብኛል” በማለት በተደጋጋሚ የምታቀርበው መከራከሪያ ኢትዮጵያ ውድቅ ስታደርገው ቆይታለች። በግድቡ መገንባት ምክንያት የሚቀንስ የውሃ ፍሰት እንደማይኖርና ይልቁንም ግብጽ ብክነት የሚስተዋልበትን የውሃ አጠቃቀሟ እንድታሻሽል በተደጋጋሚ ምክረ ሃሳብ መሰንዘሯ የሚታወሰ ነው። የውሃ እጥረት የማጋጠም ስጋት እንኳ ቢገጥማት የከርሰ ምድርና ሌሎች የውሃ አማራጮችን መጠቀም እንደምትችል በመግለጽ ጭምር።
የግብጽ መሪዎች አሁናዊ አካሄድ ሌሎች የውሃ አማራጮችና ብክነታዊ የውሃ አጠቃቀምን ማስቀረት መጀመራቸው ወደ ቀልባቸው መመለሳቸውን የሚያመላክት ይመስላል። የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ግብፃውያን በውሃ አጠቃቀም ረገድ የሚያሳዩትን አባካኝነት እንዲያስተካክሉ ቀጠን ያለ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ይህንኑ የሚያሳብቅ እርምጃ ነው። ይህ ደግሞ ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ስታቀርብ የነበረው ምክረ-ሀሳብ ትክክለኛነትን የሚያረጋግጥ ነው።
የህዳሴው ግድብ ለግብጽ የሚሰጠውን ጥቅም ጠንቅቀው የሚያውቁት ግብጽ እና ሱዳን ጉዳዩን ፖለቲካዊ ይዘት ከመስጠት ተቆጥበው ወደ ራሳቸው መለስ ብለው እንዲያዩ የሚያደርግ ነው። ግብጽ ሰሞኑን በ44.5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የውሃ ማጣሪያ በፖርት ሰይድ ከተማ የባህር ኤል ባካር ፕሮጀክትን አስገንብታ ለአገልግሎት ማብቃቷ ወደ ቀልቧ መመለሷ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
ግብጽ እና ሱዳን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ያለውን ጠቀሜታ እያወቁ የሚያቀርቡት ተቃውሞ እነሱ እንደሚሉት ጉዳት ስለሚደርስባቸው ሳይሆን ኢትዮጵያ ግድቡን መነሻ በማድረግ በአፍሪካ ቀንድ እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆና ትወጣለች ከሚል ስጋት የመነጨ መሆኑን የማህበረሰብ አንቂዋ መካ አደም ይናገራሉ፡፡
የግድቡ መገንባት የኢትዮጵያን ልማት በቀጥታ የሚደግፍ ከመሆኑ ባለፈ የአካባቢውን አገራት ከኢትዮጵያ በአነስተኛ ክፍያ የኤሌክትሪክ ሀይል እንዲያገኙ ያስችላል። በዚህም የግድቡ መገንባት በሶስቱ ሀገራት መካከል ብቻ ሳይሆን ከተቀሩት የተፋሰሱ ሀገራት ጋር ያለውን ትብብር በማሳደግ ለኢኮኖሚያዊ ውህደት መፈጠር ቁልፍ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
እንደ ማህበረሰብ አንቂዋ መካ አደም የግብጽና የሱዳን ህዝቦች የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ በፖለቲከኞቻቸው የሚነገረውን የተሳሳተ ትርክት በመረጃ አረጋግጠው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ከዚህ ሻገር ሲልም ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንዲሰሩ መሪዎቻቸው ላይ ግፊት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ነው ምክረ-ሃሳባቸውን የለገሱት፡፡
ከህዳሴ ግድቡ ትሩፋት መጠቀም የሚቻለው የቅኝ ግዛት ስምምነት ላይ በመጣበቅ ሳይሆን ወቅቱ በሚፈቅደው የትብብር፣ የንግግር እና በመርህ ላይ በተመሰረተ ድርድር ብቻ መሆኑን የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት ሊገነዘቡት ይገባል። ቅድሚያ ግን የውስጥ አማራጮችን አሟጦ መፈተሽ ጠቃሚ መሆኑን የግብጽ የሰሞኑን የውሃ ብክነት የማስቀረት ውሳኔ ማለፊያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።