ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት የአሸናፊዎች ብቻ አይሆንም

መስከረም 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) "የኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት የአሸናፊዎች ብቻ ሳይሆን ሁሉንም አሳታፊና አካታች እንዲሆን እንሰራለን" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበዓለ ሲመታቸው ላይ ባደረጉት ንግግር በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና የአገር ሉዓላዊነቶች ላይ ያተኮሩ ዋና ዋና ነጥቦችን አንስተዋል።

የእናት አገር ጥቃት የሚያንገበግባቸው ኢትዮጵያዊያን ጠላት ሲመጣ የግል ቅሬታቸውን ወደ ጎን ትተው ለአገር ሉዓላዊነት በአንድነት የሚቆሙ መሆናቸውን ገልፀው፤ "መተማመኛ፣ ደጀን፣ ጦርና ጋሻ ለሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ታላቅ አክብሮት አለኝ" ብለዋል።

"በኢትዮጵያ ስልጣን የሚያዘው በሴራና አፈሙዝ ሳይሆን በህዝብ ደምፅ ብቻ መሆኑን በ6ተኛ ጠቅላላ ምርጫ አሳይተናል" ብለዋል።

በምርጫው የተመዘገበው ድል የአንድ ፓርቲ ወይም በመንግስት ብቻ የመጣ ሳይሆን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን አሸና የሆኑበት ስለመሆኑ አንስተዋል።

"በኢትዮጵያ ለዘመናት የተከማቹ ችግሮች በአንድ ፓርቲ መሪነት ብቻ የሚፈቱ ባለመሆኑ በትብብር ለመፍታት መስራት አለብን" ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

አዲሱ መንግስት አሳታፊና አካታች አካሄድ እንደሚከተል ገልፀው፤ የፖለቲካ ስርዓቱ የአሸናዎች ብቻ ሳይሆን አካታች እንደሚሆን አስታውቀዋል።

ለዚህም አካታች ብሔራዊ የውይይት መድረክ እንደሚካሄድና ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ እንደሚፈቱ በመግለጽ በዚህ የሚያምኑ አካላትን ተሳታፊ እንደሚደረጉ ጠቁመዋል።

አሸባሪው ህወሃት በክህደትና በእብሪት እኛ የማንቆጣጠራት እና እንዳሻን የማናሽከረክራት አገር ልትኖር አይገባም ብሎ የሰሜን ዕዝ ላይ ግፍ መፈፀሙን አውስተዋል።

አሸባሪ ቡድኑ አሁንም ህፃናትን እያስታጠቀ ንፁሃንን እየረሸነ፣ አርሶ አደሩ እንደ ልጁ የሚያያቸውን እንስሳት እየገደለ በእምነት ተቋማት ላይም ጥቃት እያደረሰ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

"በዚህ ምክንያት ተገደን የኢትዮጵያን ህልውና ለማስከበር ወደ ዘመቻ መግባታችን ሊሰመርበት ይገባል" ብለዋል።

"ዋና ፀባችን አገር ሊያፈርሱ ኪሳቸውን ሊሞሉ ከተነሱ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ብቻ መሆኑ ሊታወቅልን ይገባል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ፤ ኢትዮጵያ ዛሬም የወዳጆቿን አጋርነት እንደምትሻ ገልፀው በክብሯና ሉዓላዊነቷ እንደማትደራደር አስምረውበታል።

አዲሱ መንግስት ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ጎዳና ለማሻገር ቀን ከሌት እንደሚሰራ አረጋግጠው፤ "ኢትዮጵያ ካዘመመችበት ቀና የምትልበት ጊዜው አሁን ነው" ብለዋል።

የኢኮኖሚ ጉዳይን በተመለከተም "ፍትሃዊና ፈጣን እድገት የሚያመጣ ለዜጎች ስራ ፈጣሪ እንዲሆን ለማድረግ እንሰራለን" ብለዋል።

የኑሮ ውድነት ችግርን ለመፍታት የዋጋ ንረትን ለመግታት ቅድሚያ በመስጠት እንደሚሰራ ተናግረው፤ "የኢትዮጵያዊያን አንድነት የሚፈታተነውን ጥላቻና ድህነትን ድል ለማድረግ በፅናት እንሰራለን" ሲሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም