ቀጥታ፡

አፍሪካዊያን በእናታቸው ቤት

ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምትነቷ ባሻገር የዓለማችን ጥቁር ህዝቦች ታሪክ ልዩ ስፍራ አላት። የነጻነት ትዕምርታቸው፣ የትግላቸው በኩር፣ የማንነታቸው ትንሳኤ ፈር ቀዳጅ አገር ነች። የሰው ልጆችን በቀለም በሚያበላልጠው አፓርታይድና የቅኝ ግዛት ቀንበር ለተጫነባቸው አፍሪቃዊ አገራት ደግሞ ይበልጥ ልዩ ስፍራ አላት። ምክንያቱ ለዘመናት በባርነት ቀንበር ሲማቅቁ ለነበሩ አገራት የግዛት ነጻነት፣ ሉዓላዊነትና አርነት ምሳሌ ናትና። ሰዎች በሰውነታቸው እኩል መሆናቸውን ለጥቁር ህዝቦች በተግባር አሳይታለች።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊያን ነጻነት ደጀን፣ ነጻ ለወጡት ደግሞ የጋራ ማህበራቸው መሰብሰቢያ ማማቸው ነች። በዚህም በርካታ አገራት የሰንደቅ ዓላማዋን ቀለማት ተሻምተዋል፤ የትግል ስልቷን ቀስመዋል፤ የመጀመሪዋ የመንግስታቱ ማህበር አባል አፍሪካዊት አገር መሆኗ፣ ለአፍሪካ  አንድነት ድርጅቶች ግንባር ቀደም መስራችና የአፍሪካዊያን ማህበር መገኛ በመሆኗም ለአፍሪካዊያን እናታቸው ወይም የመሰብሰቢያ ቤታቸው ናት።

በየዘመናቱ የነበሩ መሪዎቿም ለፓን-አፍሪካዊነት ማንነት ማደግ፣ አፍሪካን ለአፍሪካዊያን ንቃናቄ አቀንቃኞች በመሆናቸው አፍሪካዊያን በልባቸው ለኢትዮጵያ ልዩ ስፍራ አላቸው። ይህም ዛሬም አለ በአፍሪካ መሪዎች ዘንድ የኢትዮጵያ የትንናት  ከፍታ፣ ለአፍሪካውያን የዋለችው ውለታ አልተዘነጋም። ይህም ዛሬም በመስቀል አደባባይ ተገኝተው በመንግሰት ምስረታ በዓለ ሲመት ላይ የታደሙ የአፍሪካ መሪዎች በአንደበታቸው አረጋገጠዋል፤ 'ታላቋ እናታችን ኢትዮጵያ' ሲሉ ትናንትን ዋጅተው፤ የነገዋን ቸር ውሎ አዳሯን መሻታቸውን ገልጸዋል። ከየመጡበት የአፍሪካ ማዕዘናት ህዝባችውን ወክለው ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም መልካም የስራ ዘመንና የእንኳን ደስ አለህ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአፍሪቃዊነት አቀንቃኙ አንገፋው ፖለቲከኛ የዩጋንዳ ፕሬዚዳነት ዩሮ ሞሶቬኒ በኢትዮጵያ አጋርነታቸውና የምዕራባዊያን ሴራ ተቃዋሚነታቸው ጎልተው ይነሳሉ። ስለነገዋ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዳይ ያሳሰባቸው ሞሶቬኒ በዛሬው የእንኳን ደስ አላችሁ መልክታቸውም የአገራቸውን ተሞክሮ አንሰተው አጠይቀዋል። ላለፉት 60 ዓመታት ብዙ ነገሮችን በአፍሪካ መታዘባቸውን የገለጹት ፕሬዝንዳነቱ፤ "በአፍሪካ የቸገረን ነገር ቢኖር የዘውግ ወይም ማንነት ተኮር ፖለቲካ ነበር" ብለዋል።

"ሃይማኖትንና የነገድ ፖለቲካ ትልቅ ተግዳሮት ነው" ያሉት ሞሶቬኒ፤ ኢትዮጵያዊያን በተናጠል ሳይሆን በጋራ ማንነታቸው በኢትዮጵያዊነት መንፈስ በጥቅም ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ማራመድ እንዳለባቸው ለመምከር ይመስል "የፍላጎት ወይም ዘውግ ተኮር ትመርጣለች?" ሲሉ አጠይቀዋል።

የታላቁ የፓን አፍሪካ አቀነቃኝና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራች የጆሞ ኬንያታ ልጅ የወቅቱ የጎረቤት አገር ኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ደግሞ አመጣጣቸው ህዝባቸውን ወክለው ደስታቸውን ለመግለጽ፣ ለኢትዮጵያ አጋርነታቸውን ለማሳየት ስለመሆኑ አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ "የኢትዮጵያን ህዝብ ለመምራት፣ ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ፣ ህዝቦቿን ወደ አንድነትና መቀራረብ ለማምጣት በህዝቡ ትልቅ ሃላፊነት ተጥሎብሃል" ያሉ ኬንያታ፤ ይህን የታሪካዊ አገር ህዝብ ወደአንድነት ለማምጣት "ምኞቴም ጸሎቴም ነው" ብለዋል።

"ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት እናት፣ ኢትዮጵያ ብቸኛዋ ለቅኝ ግዛት ያልተንበረከከች አገር፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊያን አገራት የነጻነት ደጀን የሆነች አገር፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ  አገራት እናት አገር ነች" ሲሉም ገልጸዋታል።

"እናት ሰላሟ ካልተረጋገጠ ደግሞ ቤተሰቡ ሰላም አይሆንም" ያሉት ኬንያታ፤ "ሰላምና መረጋጋቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያ፣ የበለጸገች አፍሪካ እውን እንድትሆን በቁርጠኝነት እንድትሰራ፤ ፈጣሪም ለዚህ እንዲረዳህ እመኛለሁ" ብለዋል።

በአማርኛ ቋንቋ "ኢትዮጵያ ለዘላላም ትኑር" በማለት ታዳሚውን በደስታ ያስጮኹት የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ ደግሞ የቀድሞዋ የአብሲኒያ ግዛተ አፄ ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራችና መቀመጫ፣ ቀዳሚዋ አፍሪካዊት የመንግስታቱ ማህበር አባል የሆነች ታሪካዊት አገር ስለመሆኗ፤ በቅርብ ዓመታት ደግሞ በፈጣን በልማት ጎዳና ላይ የነበረች በተለይም ለአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ተምሳሌታዊ አገር መሆኗን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በረጅም ዘመኗ ታሪኳ በርካታ ፈተናዎች ቢያጋጠማትም ፈተናዎቿ እያጠናከሯት የመጣች አገር፤ ህዝቦቿም በጋራ ትግል አንድነታቸውን ያስጠበቁ፣ ሰላሟን በራሷ እያሰፈነች እየተጠናከረች የዘለቀች አገር መሆኗን መስክረዋል። ኢትዮጵያ አፍሪካዊያን ችግርና መከፋፈል ሲገጥማቸው በሰላምና በውይይት ለመፍታት የሚሰባሰቡባት አገር መሆኗን አንስተዋል። ኢትዮጵያ ምን ጊዜም የጋራ የአንድነት ምሳሌ ስለመሆኗ ተናግረዋል።

"ምንም ችግር ቢገጥማት ኢትዮጵያ ይበልጥ ትጠናከራለች" ያሉት ኦማር ጊሌ፤  በርግጥም ኢትዮጵያዊያን ከዚህ በላይ አንድነታቸውንና ብዝሃንነታችውን ጠብቅው ስኬታማ ዕድገት እንደሚያስመዘግቡ እምነታቸውን ነው የገለጹት። ኢትዮጵያዊያን አሁናዊ ችግሮችን ተወጥተው አሸናፊ እንደሚሆኑ ተስፋቸውን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ፣ ህዝቦቿን በእርቅና በሰላም እንዲኖሩና እንዲለሙ የጎረቤት አገር ጅቡቲ መንግስትና ህዝብምን ያልተቆጠበ ድጋፍ ያደርጋል ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጣይ ጉዞ መልካም ምኞታቸውን አሳውቀዋል።

ሌላው የአዲሲቷ አገር ደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማርዲያት "ኢትዮጵያ ችግር ሲገጥመን ሩጠን የምንገባባት የችግራችን ሁሉ ደራሽ ታላቋ እናታችን" ብለዋታል። አገራቸው ደቡብ ሱዳን ነጻነቷን እንድታረጋግጥና ሰላሟ እንዲጠበቅ ከቀዳማዊ አፄ ሃይለስላሴ ጀምሮ የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎች ያልተቆጠበ ድጋፍ ስለማድረጋቸው ተናግረዋል። ካለኢትዮጵያ ድጋፍ ደቡብ ሱዳን ዛሬዋን ማንነቷን ዕውን ማድረግ ይሳናት እንደነበር ገልጸው፤ "ኢትዮጵያዊያን በውስጣዊ የግዛት አንድነት ችግር ውስጥ ሆና ስንኳ ብቻችንን አልተወችንም" ሲሉ ውለታዋን ዘክረዋል። ኢትዮጵያዊያን "ምንጊዜም የትምና ምንም ቢያጋጥማችሁ ከጎናችሁ ነን፤ ታናሽ ወንድሜ አቢይ አህመድ እንኳን ደስ አለህ" ብለዋል።

የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ሞሐመድ ለአፍሪካ ቀንድ አገራት የራስ ምታት የሆነውን ጉዳይ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ኢትዮጵያ የነበራትን ሚና አልዘነጉም። አገራት የሚገጥማቸውን ችግር ለማለፍ ከመሪዎች የመፍትሄ እርምጃ መውሰድ እንደሚያሻ ገልፀው፤ "አፍሪካዊያን መሪዎች ስለ የጋራ ነጋችን ልንሰራ ይገባል" ብለዋል። ዶክተር አቢይ አህመድ መሪነት የአገሩን ልማት እንደሚያረጋግጥና የመራጮችን ተስፋ እውን እንደሚያደርግ እምነታቸውን ገልጸዋል። "ኢትዮጵያና ሶማሊያ ሽብርተኝነትን በጋራ እንደሚዋጉት ሁሉ በአፍሪካ ቀንድ የጋራ ልማትና ብልጽግና ለማረጋገጥ ከአዲሱ መንግስት ጋር እንሰራለን" ብለዋል። ለዚህ ደግሞ በአቢይ አህመድ መሪነት ይሳካል የሚል ተስፋቸውን ገልጸዋል።

በአፍሪካ አህጉር በህዘብ ብዛቷ ቀዳሚ የሆነችው ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ናይጀሪያ ፕሬዝዳንት ሌላው የበዓል ሲመቱ ክብር እንግዳ ነበሩ። የኢትዮጵያ ጉዳይ የሁሉም አፍሪካዊያን ጉዳይ መሆኑን ገልጸው፤ ሁሉም የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ለኢትዮጵያ ጥቅም፣ አንድነትና ሰላም በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባችው መክረዋል። ናይጄሪያና ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ግንኙናታቸውን በማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል። "የኢትዮጵያ ግዛት አንድነት እንዲጠበቅና ሰላሟ እንዲረጋገጥ የናይጄሪያ ህዝብና መንግስት ኢትዮጵያን ይደግፋል፤ ፈጣሪ ኢትዮጵያና ናይጄሪያን ይጠብቅ" ሲሉ መልካም መሻታቸውን አንጸባርቀዋል።  

የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል እና የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስትር ጂን-ሚሼል ሳማ ሉኮንዴም በጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓለ ሲመቱ ላይ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም