ቀጥታ፡

የጋዜጠኛ ጋሻው ጫኔ ሥርዓተ ቀብር ተፈፀመ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 24/2014(ኢዜአ) የቀድሞው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋዜጠኛ ጋሻው ጫኔ ሥርዓተ ቀብር በአዲስ አበባ ብሔረ ጽጌ ማርያም ዛሬ ተፈጽሟል።

ጋዜጠኛ ጋሻው ጫኔ ከአባታቸው ከአቶ ጫኔ ብዙነህ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ የሺመቤት ታዬ በቀድሞው ኢሉባቦር ክፍለ ሃገር መቱ ከተማ በ1956 ዓ.ም ነው የተወለዱት።

የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በትውልድ ቦታቸው መቱ ተከታትለው በ1974 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን አጠናቋል።

ጋዜጠኛ ጋሻው ጫኔ በከፍተኛ ትምህርት ዝግጅቱ በ1975 ዓ.ም ከመቱ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ኮሌጅ በህንጻ ቴክኖሎጂ ዲፕሎማ፤ በመቀጠልም በ1993 ዓ.ም በህትመት ጋዜጠኝነት በዲፕሎማ ተመርቋል።

በ1999 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጆርናሊዝምና ኮሙኒኬሽን በመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በ2001 ዓ.ም ሁለተኛ ዲግሪውን ህንድ ከሚገኘው ኢንድራ ጋንዲ ዩኒቨርሲቲ በሶሲዮሎጂ የትምህርት ዘርፍ ተቀብሏል።

የቤተሰቡ አራተኛ ልጅ የሆነው ጋዜጠኛ ጋሻው ጫኔ ከልጅነቱ ጀምሮ የመፃፍ ዝንባሌ ስለነበረው ገና በአፍላ ዕድሜው የጋዜጠኝነት ሙያን ተቀላቅሎ ከ35 ዓመታት በላይ በሙያው ሰርቷል።

በ1976 ዓ.ም በቀድሞው የማስታወቂያ ሚኒስቴር መቱ ቅርንጫፍ ዋና ወኪል በመሆን ስራ የጀመረ ሲሆን ከዚያም ወደ ጋምቤላ ቅርንጫፍ በመዛወር በዋና የዜና ወኪልነት እስከ 1985 ዓ.ም አገልግሏል።

በ1985 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና መስሪያ ቤት በመዛወር እስከ 1990 ዓ.ም በሪፖርተርነት ያገለገለ ሲሆን ራሱን በትምህርትና በልምድ በማብቃት ከ1990 ዓ.ም እስከ ከ1993 ዓ.ም ረዳት አዘጋጅ በመሆን አገልግሏል።

ከ1993 እስከ 1999 ዓ.ም በአዘጋጅነት፣ ከ1999 እስከ 2001 ዓ.ም የሬዲዮና ቴሌሌቭዥን ፕሮግራም ፕሮዳክሽን ኤክስፐርት ሆኖ ሲሰራ ከቆየ በኋላ፤ በ2001 ዓ.ም ወደ ቀድሞው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ተዛውሮ እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ የአገር ውስጥ ቋንቋዎች ከፍተኛ ኤክስፐርት፤ ከ2010 እስከ 2011 ዓ.ም የአገር ውስጥ ቋንቋዎች ዋና አዘጋጅ በመሆን አገልግሏል።

በ2011 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በመዛወር ህይወቱ እስካለፈበት መስከረም 23 ቀን 2014 ዓ.ም በምክትል ዋና አዘጋጅነት እና በከፍተኛ ኤክስፐርትነት ሲያገለግል ነበር።

ጋዜጠኛ ጋሻው ጫኔ ለስነ-ጽሁፍና ጋዜጠኝነት ባለው ዝንባሌ በጋዜጠኝነት ከመቀጠሩ ቀደም ብሎም በተለይ በኢትዮጵያ ሬዲዮ እሁድ ፕሮግራም ማህበራዊ ጉዳዮችን በማንሳት የተለያዩ መጣጥፎችን በማቅረብ ይታወቃል።

በስፖርቱም ዘርፍ ብቃት የነበረው ጋዜጠኛ ጋሻው ጫኔ የኢሉባቡር ክፍለ ሃገርን በእግር ኳስ በመወከል በኢትዮጵያ ትቅደም ዋንጫ ጨዋታዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ጋዜጠኛ ጋሻው በስራ ቆይታው በተለይም የማህበረሰብ ችግሮችን በመፈተሽና ለችግሮቹ መፍትሄ በመጠቆም ያቀርባቸው የነበሩ ዘገባዎች የበርካቶች መነጋገሪያ የሆኑ እንደነበሩ ይታወሳል። በዚህም ለሌሎች ጋዜጠኞች ምሳሌ በመሆን ይታወቃል።

ጋዜጠኛ ጋሻው በባህሪው ሰው አክባሪ፣ ሩህሩህና አዛኝ ያለውን አካፋይ፣ ጨዋታ አዋቂ በመሆኑ በስራ ባልደረቦቹና በጓደኞቹ የተወደደ ነበር።

ጋዜጠኛ ጋሻው ባለትዳር ነበር።

ጋዜጠኛ ጋሻው ባጋጠመው ድንገተኛ ሕመም ትናንት ከዚህ ዓለም ተለይቷል፤ የቀብር ስነ-ሥርዓቱም ዛሬ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ብሔረ ፅጌ ማሪያም ቤተ-ክረስቲያን ተፈጽሟል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በጋዜጠኛ ጋሻው ጫኔ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቹና ወዳጅ ዘመዶቹ መፅናናትን ተመኝቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም