ቀጥታ፡

የተመሰረተው መንግሥት አገሩን በማልማት ራዕይ ያለው ሕዝብ እንዲፈጠር ሊሰራ ይገባል

መስከረም 24/2014 (ኢዜአ) የተመሰረተው መንግሥት አገሩን በማልማት ራዕይ ያለው ሕዝብ እንዲፈጠር ሊሰራ እንደሚገባ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።

አስተያየት ሰጪዎቹ ዶክተር አቢይ አህመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በመመረጣቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምስረታ ጉባኤውን ሲያካሂድ ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሾሟል።

ይህን ተከትሎም ኢዜአ በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ነዋሪዎች በመንግሥት ምስረታው የተሰማቸውን ስሜት ጠይቋል።

አቶ አዲልካሰው ተስፋዬ የዶክተር አቢይ አህመድ መመረጥ ትልቅ ደስታ እንደፈጠረላቸው ገልጸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቷ የሚስተዋሉ ችግሮችን እንደሚፈቱ ያላቸውን ሙሉ እምነት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የተበደለችውን በአምስት ዓመት ይክሳሉ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ርስቱ ተስፋዬ በመንግሥት ምስረታው የተሰማውን ደስታ ገልጾ፤ አዲሱ መንግሥት ለወቅታዊ ጉዳዮች እልባት መስጠት ይኖርበታል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን አንድነት ለማጠናከር የሚሰሯቸውን ሥራዎችን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ያለው ወጣት ፍሬዘር ደሳለኝም እስከታችኛው መዋቅር በመውረድ ሊተገበሩ  የሚገባቸው ጉዳዮች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ነው ያለው። 

መንግሥት ራዕይ ያለው ትውልድ ለመፍጠር መሥራት አለበት ያለው ደግሞ አባይ ተክልዬ ነው።

ሰዎች በላባቸው ሰርተው ለማደር በቂ መደላደል መፈጠር እንዳለበትም ነው ያመለከተው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም