ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ችግሮቿን በጥንካሬ ትወጣለች

መስከረም 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) “ኢትዮጵያ እየገጠሟት ያሉትን ችግሮች በጥንካሬ ትወጣለች” ሲሉ የጂቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ ገለጹ።

በመስቀል አደባበይ እየተካሄደ ባለው የመንግስት ምስረታ ስነ-ስርዓትና በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በዓለ ሲመት ላይ የተለያዩ የአፍሪካ አገር መሪዎች ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

የጂቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ ኢትዮጵያ የሚያጋጥሟትን ችግሮች በድል ተወጥታ በጥንካሬዋ እንደምትቀጥል ተናግረዋል፡፡

የጅቡቲው ፕሬዚዳንት “ዛሬ እዚህ በመገኘቴ ተደስቻለሁ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር አቢይና ለኢትዮጵያ ህዝብ የጅቡቲን ህዝብ በመወከል ደስታየን እገልፃለሁ” ብለዋል፡፡

“ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካ ጉዳይን ከ1920 ዎቹ ጀምሮ በማንሳት ቀዳሚ ናት” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ኢትዮጵያ እያዝመዘገበችው ያለው እድገት ለቀጠናውና ለአህጉሩ ምሳሌ መሆኑን ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያ እያለፈችበት ያለውን ውጣ ውረድ ተወጥታ በጥንካሬ ትቀጥላለች” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የቀጣናውን ሰላም አስተማማኝ ደረጃ ላይ እንዲደርስ መተባበር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር በበኩላቸው ባስተላለፉት መልእክት ደቡብ ሱዳን ድጋፍ በፈለገችበት ወቅት ሁሉ ኢትዮጵያ ቀድማ እንደምትደርስ ታሪክን በማስታወስ ገልጸዋል።

በመሆኑም ደቡብ ሱዳን ምንጊዜም ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅ ሆና እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

ለኢትዮጵያ ህዝብና ለጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ እንኳን ደስ ያላችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል።

“የኢትዮጵያ ህዝቦች ያለእናንተ ድምጽ ይህ ድል አልመጣም፣ እዚህ የተገኘሁት ኢትዮጵያ ትልቅ እናታችን በመሆኗ ነው” ብለዋል።

“የኢትዮጵያ ህዝቦች በምታደርጉት ጉዞ ሁሉ አብረናችሁ ነን” ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሬ ሙሰቬኒ የኡጋንዳ ህዝብ ለኢትዮጵያ ያለውን ክብር ገልጸዋል።

የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአህጉሩ የነጻነት ተምሳሌት የሆነች ታላቅ እናት ስለመሆኗ ተናግረዋል።

የአፍሪካ እናት ኢትዮጵያ ሰላም ከሌላት ሁሉም የአፍሪካ አገር ሰላምሊሆን እንደማይችል ሰው፤ ለኢትዮጵያ ሰላም መሆን ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም