ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩና አፈ ጉባዔያቱ


መስከረም 24/2014 (ኢዜአ) ላለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ መልከ ብዙ አገራዊ ቀውሶች ያስተናገደችበት ወቅቶች ነበሩ።

ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ 27 ዓመታት መንግስታዊ ሽብር ተግባር ላይ ተሰማርቶ አገራዊ አንድነትን አደጋ ላይ የጣለው የአሸባሪው ሕወሃት መራሹ ስርዓት በህዝባዊ ማዕበል ተወግዶ በ2010 ዓ.ም ህዝብ የደገፈው አመራር ተተካ።

ያም ሆኖ በህዝብ ማዕበል ከስልጣን የተገፋው የአሸባሪው ሕወሃት ቡድን የለውጥ መንግስቱን ለመፈታተን የቀደመ መዋቅሩን በመጠቀም በመላ አገሪቷ ባደረገው የግጭትና የጥፋት ማዕከል እንዲሆን አበክሮ መስራቱን ተያያዘው።

በዚህም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጨምሮ ዓይነተ ብዙ አገራዊ የጸጥታ ችግሮች መኖራቸው ደግሞ ሕግ መንግስታዊ ትርጓሜ ተደርጎ ለስድስተኛው ዙር አገር አቀፍ ምርጫ ለአንድ ዓመት እንዲራመዝ ግድ ሆኗል።

አሸባሪው ሕወሃት አገር ለማፍረስ የጀመረውን ጦርነት ጨምሮ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎች በበረቱበት፣ የአገር ሕልውና ዘመቻ በታወጀበት ባለፈው ወርኃ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ኢትዮጵያ በታሪኳ "ህዝብ በነቂስ ውጥቶ ይመራኛል" ብሎ ላመነበት ፓርቲ ድምጹን የሰጠበት አገራዊ ምርጫ ተከውኗል።

ይህን ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ በምርጫው ያሸነፈው የብልፅግና ፓርቲ በዛሬው ዕለት መስከረም 24 ቀን መንግስት ምስረታውን በይፋ አካሂዷል።

ብዙሃኑ በጉጉት ሲጠብቁት የቆየው ለቀጣይ አምስት ዓመታት ኢትዮጵያን የሚመራው በህዝብ የተወከለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መስራች ጉባዔው የምክር ቤቱን አፈ ጉባዔና ምክትል አፈ ጉባዔን ሰይሟል፤ ፓርቲው ያቀረበውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሹመትም አጽድቋል።

በዚህም ላለፉት የለውጥ ዓመታት በርዕሰ መንግስትነት የቆዩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ በነበራቸው ሃላፊነት እንዲቀጥሉ ድጋሚ ተመርጠዋል። ምክትል አፈ ጉባዔነት ደግሞ ወይዘሮ ሎሚ በዶ ተሹመዋል። የአዲሱ መንግስት ተሿሚዎች በቀጣይ አምስት ዓመታት ኢትዮጵያን በተሰጠው ኅላፊነት ለመምራት ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

በህዝብ ዘንድ የረዘም እውቅያ ያልነበራቸው ዐቢይ አህመድ (ፒ ኤች ዲ) በለውጡ መባቻ ሰሞን በአጭር ጊዜ ያገኙት እውቅና ድጋፍ አገሪቷን እንዲመሩ ያገኙት ተቀባይነት አግራሞት ያጫረ ነበር። በዚህም መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ሲሾሙ ህዝባዊ ቅቡልነት ከፍተኛ ነበር።  

በተሾሙበት ዕለት  በምክር ቤቱ አዳራሽ ባሰሙት የ35 ደቂቃዎች  ቀዳሚ ንግግራቸው የኢትዮጵያዊነትን ከፍታ ያጎሉበት፣ በፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያደርጓቸው ለውጦች በተለይም ሁለት አስርት ዓመታትን የፈጀውን የኤርትራ የውጭ ግንኙነት ለማደስ መሻታቸውን የገለጹበት ነበር። ይህም በርግጥም ኢትዮጵያዊያን ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከልብ የመነጨ ድጋፋቸውን የቸሩበት ቅጽበት ነበር።

በንግግራቸው "በተለያየ ጊዜ መስዋዕትነት ለከፈሉ የመብት ተከራካሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ በቅጡ ሳይቦርቁ ህይወታቸው ለተቀጠፈ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች ለሥነ ልቦናዊና አካላዊ ጉዳት ለተዳረጉ ቤተሰቦችና ግለሰቦች ከልብ የመነጨ ይቅርታ እጠይቃለሁ" በማለትም በኢህአዴግ ስርዓተ መንግስት ለተፈጸሙ መንግስታዊ ግፎች ያሰሙት የይቅርታ ንግግርም ሌላው ህዝብ በነቂስ ወጥቶ እንዲደግፋቸው ሰበብ ነበር። በጠቅላይ ሚኒስትር ሃላፊነት በመጡ በሳምንታት ውስጥም መጠነ ሰፊ ለውጦችን በተግባር ያሳዩ ሲሆን፤ በተለይም "በይቅርታና በፍቅር መደመር" የሚል በተደጋጋሚ ከአንደበታቸው የማይለይ ጽንሰ ሃሳብ ገቢራዊ ማድረግ ጀመሩ።

ከነዚህም መካከል አንዱም የመገናኛ ብዙሀን ነጻነት እና የፖለቲካ እስረኞች መፈታት ነበር። በፖለቲካዊ ምክንያት የታሰሩ ግለሰቦች ከእስር ተፈቱ፤ በውጪ አገር ነፍጥ ያነገቡ በአሸባሪነት የተፈርጁ ድርጅቶች የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቶ ወደ አገር ቤት ገቡ፤ ኢትዮጵያ የታሰረ ጋዜጠኛ የሌለባት አገር የተባለችበት ዘገባ እስኪወጣ ድረስ ለዓመታት በጋዜጠኝነታቸው ብቻ የታሰሩ ባለሙያዎች ከግፍ እስር ተፈቱ። ይህም ዓለም አቀፍ ተቋማትን ጨምሮ የዲሞክራሲ ተቋማትና መንግስታት ጠቅላይ ሚኒሰትሩን "ጎሽ አበጁ" አስብሏቸዋል።

ከወራት በፊት አመፅ ብቻ የሚያስተናግዱ አደባባዮች፤ ወደ ድጋፍ ሰልፍ አስተናጋጅነት ተለወጡ። ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፋቸውን ለመግለጽ በነቂስ የወጡ አዲስ አበቤዎችም ቦንብ የተወረወረባቸው በዚህ ኩነት ነበር። ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፍ በአገር ወስጥ ብቻ ሳይሆን በተቃውሞ ጎራ የሚታወቀው የዳያስፖራ ማህበረሰብም 'አጃይብ' እስኪያሰኝ ድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አጋርነቱን አሳይቷል። ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ ልሂቃንና ምሁራን ከአዲሱ የለውጥ መንግስት ጋር በጋራ ለመስራት ሳያቅማሙ ወደአገር ቤት የገቡትም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ነበር።

በተለይም በትርምስ ጫፍ ላይ የነበረች ኢትዮጵያ አዲስ ተስፋ ሰንቃ ለቀጣናው ሠላምና መረጋጋት ሁነኛ ተጫዋች ሆነች። የኢትዮ-ኤርትራ እርቅ በደም የተሳሰሩ ህዝቦች ዳግም ግንኙነት የሁለቱን አገራት ዜጎች እንባ ያራጨ አጋጣሚ ነበር። በጎረቤት አገራት መንግስታት ጋር የመሰረቱት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙንትም አዲስ መልክ የያዘ ነበር። ይህም ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ ኤርትራን የጎበኙ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ መሪ የሆኑት ዶክተር ዐብይ አህመድ የዓለም ሰላም ኖቬል ተሸላሚ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ አድርጓቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መልከ ብዙ እርምጃዎች ቢወስዱም ቅሉ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ባሉት ሶስት ዓመታት ፈተናዎች ብርቱ ነበሩ። አገር በማተራመስና የለውጥ መንግስት በማዳከም ወደማዕከላዊ ስልጣን ለመመለስ የፈለገው የአሸባሪው ህወሃት መንግስት አገራዊ ሆኖ ከተዋቀረው ፓርቲ ራሱን ማግለሉን ጨምሮ የመላ አገሩቱ ግጭቶች የጀርባ ተዋናይ ሆኖ ቀጠለ። በአገሪቷ ማዕዘናት ሁሉ ንጹሃንን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች የበረቱበት፣ ንጹሃን ሕይወት የተቀጠፈበትና ንብረት የወደመበት፣ ሚሊየኖች የተፈናቀሉበት ፈታኝ ዓመታት ነበሩ።

ከዚህም በተጨማሪ በአሸባሪው ሕወሃት አመራር የሙስና ምንጭ ሆኖ ተስተጓጉሎ የነበረው ኢትዮጵያዊያን "የሰንደቅ ዓላማ ፕሮጀክታችን" የሚሉት የታላቁ ህዳሴ ግድብ አዲስ የፖለቲካ ጉዳይ ተድረጎ በዓለም መድረክ ኢትዮጵያ የተፈተነችበት ወቅትም ነበር። በድርድር ሂደትም፤ በግድቡ ግንባታ ቀጣይነትና ውሃ ሙሌት ብስራት ዕውን ይዞ ቢመጣም ቅሉ።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም አሸባሪው ቡድን በአገር መከላከያ ላይ ጥቃት በመፈጸም ወደ ስልጣን ለመምጣት ያደረሰው ጥቃትና አገሪቷን ህልውና አደጋ ውስጥ የጣለበት አጋጣሚም ሌላው ፈተና ነበር። በዚህ ሰበብም በኢትዮጵያ ውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ በመግባት መፈትፈት የለመዱ የውጭ ሃይላት እድሉ በመጠቀም ኢትዮጵያ ላይ ጫና ያበረቱበት ወቅት ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት የጀመሩት አገራዊ ፖለሲ ማሻሻዎች መካከል በመደመር ጽንሰ ሃሳብ አሳታፉ ፖለቲካዊ ስርዓት መገንባት፣ አገራዊ ኢትዮጵያዊነትን ማጎልበት፣ አገር በቀል ኢኮኖሚ ፖሊሲ መቅረጽ፣ አረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር እና የኢትዮጵያን ጸጋዎች ወደ ኢኮኖሚ የመለውጥ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት እንቅስቃሴም ድጋፍ ያስገኘላቸው ሌላው አቢይ ጉዳይ ነበር። ይህ ግን በተለይም ደካማና ተላላኪ የኢትዮጵያ መንግስት እንዲመሰረት የሚሹ የምዕራባዊያን ሃይላት የራስ ምታት በመሆኑ በኢትዮጵያ ላይ ሰበብ እየደረደሩ መልከ ብዙ ጫናዎችን ያበዙበት ዓመታትም ነበር።

በዚህ ፈታኝ ወቅቶች አይሰምርም የተባለው አገራዊ ምርጫም ከወትሮ በተለዬ ታአሚኒ፣ ፍትሃዊና ህዝባዊ ምርጫ ተብሎ የተወደሰ፤ 'ኢትዮጵያ አሸነፈች' የተባለለት ምርጫ ሆነ። በእነዚህ መጠነ ሰፊ ፈተናዎች ውስጥ ምርጫዋን ያካሄደችው ኢትዮጵያም በምርጫው ውጤት መሰረት ዛሬ አዲስ መንግስት መስርታለች።

አዲሱ መንግስትም በግል የተወዳደሩ፣ በተፎካካሪ ፓርቲነት የተሰለፉ አባላት ያካተተው የሕግ አውጭ አካል የሆነው ምክር ቤትም የምስረታ ጉባኤውን ዛሬ ሲያካሂድ መጋቢት 24 ወደ መንበረ ስልጣን የወጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ዛሬ መስከረም 24 ድጋሚ በጠቅላይ ሚኒስትርነት አጽድቋል። ላለፉት ሶስት ዓመታት ኢትዮጵያን የመሩት ዶክተር ዐብይ አህመድ ስልጣናቸውን ለቀጣይ አምስት ዓመታት እንዲያራዝሙ ይሁንታ ተሰጥቷቸዋል።

ላለፉት ጥቂት ዓመታት በነበሩ ፈተናዎች ሁሉ የነበሩት፣ አፈንጋጩ የሕወሃት ቡድን በአሸባሪነት ሲፈረጅ በምክር ቤት አፈ ጉባዔነት የመሩት አቶ ታገሰ ጫፎም ምክር ቤቱ ዳግም በቀድሞው ሃላፊነታቸው እንዲቀጥሉ መርጧቸዋል። ላለፉት ሶስት ዓመታት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በደቡብ ክልል ከወረዳ አመራርነት እስከ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንትነት፣ በሚኒስትር ዴኤታነትና ሚኒስትርነት አገራቸውን አገልግለዋል። በእስካሁን የመንግስት ሃላፊነታቸውም የተሻለ ለውጥ እንዲፈፀም የጎላ አስተዋፅኦ ስለማድረጋቸው ተጠቅሷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ከአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደርነት በቅርቡ የተነሱት አቶ አገኘሁ ተሻገር ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሆነው ተሹመዋል። አቶ አገኘሁ ተሻገር ከክልል ርዕሰ መስተዳድረነታቸው ቀደም ብሎም በአማራ ክልል አመራር አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር፣ የክልሉ ንግድ ቢሮ፣ በሠላምና የጸጥታ ቢሮና በሌሎች ሃላፊነቶች አገልግለዋል።

በኦሮሚያ ክልል አፈ ጉባኤነት፣ በባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊነት እና በሌሎች ሃላፊነቶች ያገለገሉት ወይዘሮ ለሚ በዶ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ሆነዋል። በአፋር ክልል የተለያዩ የክልል ተቋማት በሃላፊነት ያገለገሉት ወይዘሮ ዘሃራ ዑመድ ደግሞ የፌዴራሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሆነዋል። በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የአዲሱ መንግስት ምስረታም በይፋ ተከናውኗል። የጠቅላይ ሚኒስትሩን በዓለ ሲመት ለመታደምም የበርካታ ወዳጅ አገራታ መሪዎች በአፍሪካ ርዕሰ መዲናዋ አዲስ አበባ ገብተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም