ቀጥታ፡

የተመሰረተው መንግስት አስተማማኝ ሰላምና አንድነትን ያስፍናል የሚል ተስፋ አለን

ደሴ ፤ መስከረም 24/2014 (ኢዜአ) አዲስ የተመሰረተው መንግስት አስተማማኝ ሰላምና አንድነት ከማስፈን ባለፈ የኑሮ ውድነቱን ያረጋጋል ብለን እንጠብቃለን ሲሉ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ነዋሪዎቹ በመንግስት ምስረታው  ለተሾሙ  ወኪሎችም  መልካም የስራ ዘመን ተመኝተዋል፡፡

በደሴ   የመናፈሻ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ከበደ መሸሻ ለኢዜአ እንዳሉት፤  ተዋዶና ተዋልዶ በፍቅር የሚኖረውን ህዝብ አሸባሪው ህወሓት  እርስ በርሱ እንዲጠራጠርና እንዳይተማመን ሲያሴር ቆይቷል፡፡

ህብረተሰቡንም በዘርና ሐይማኖት በመከፋፈል እርስ በእርስ እንዲጠፋፋ ያላደረገው ሙከራ ባይኖርም ምኞቱ ሳይሳካ ከመቅረቱም ባለፈ ሴራው መልሶ እራሱን እያጠፋው ነው ያሉት፡፡

''ዛሬ በአዲስ የተመሰረተው መንግስት ቡድኑ ለ27 ዓመታት ከውጭ ጠላቶቻችን ጋር ተባብሮ የፈጠረውን ውስብስብ ችግርና የኢኮኖሚ አሻጥር በመቀልበስ አስተማማኝ ሰላምና አንድነት ይፈጥራል ብዬ እጠብቃለሁ'' ብለዋል፡፡

ከድሃ አቅም በላይ የሆነውን የኑሮ ውድነትም ከማስተካከል ባለፈ በቤት ኪራይ ለሚሰቃዩ ወገኖች የመኖሪያ ቤትና ቦታ ሊያመቻች  እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

በቀጣይ በሚካሄዱ ሹመቶች አቅም ያላቸውን ሀገርና ህዝብ ወዳድ የተፎካካሪ ፓርቲዎችን አባላትንም በማሳተፍ አቅም ፈጥሮ ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ ምዕራፍ ያሸጋግራል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡

የሆጤ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት አዜብ ሰይፉ በበኩሏ፤  አዲስ የተመሰረተው መንግስት ሀገር ለማፍረስ የሚፍጨረጨረውን አሸባሪ ቡድን እንዳይነሳ አድርጎ በመቅበር የህዝብን እምባ ያብሳል ብዬ እጠብቃለሁ ብላለች፡፡

ከምንም በላይ እንቅልፍ የነሳንን ሰላም አረጋግጦ በየትኛውም አካባቢ ያለ ስጋት መንቀሳቀስ እንድንችል ከማድረግ ባለፈ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ነጻነት ማስጠበቅ የመጀመሪያው ተግባሩ ለሆን ይገባል ስትል ገልጻለች።

ለወጣቱ የስራ እድል መፍጠርና  የኑሮ ውድነት ማረጋጋትም ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው ያለችው ወጣቷ፤ በማንኛውም ጉዳይ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ  የኢትዮጵያ ብልፅግና እውን ለማድረግ የድርሻዋን እንደምትወጣ ተናግራለች፡፡

''አዲሱ መንግስት ህብረተሰቡን አሳትፎ አሸባሪውን ቡድን ዳግም ስጋት በማይሆን መልኩ ደምስሶና ሰላም አስፍኖ በፍጥነት ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ይመልሳል'' የሚል እምነት አለኝ ያሉት ደግሞ የመናፈሻ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ብርሃኑ አዲስ ናቸው፡፡

ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ምሁራንንም አሳትፎ ኢትዮጵያን ከገጠማት ውስብስብ ችግር በአጭር ጊዜ በማላቀቅ ሉዓላዊነቷን አስጠብቆ ወደ ዘላቂ ሰላምና ልማት የመመለስ ኃላፊነትንም ተሸክሟል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላምና አንድነት እዲሰፍን ብሎም የኑሮ ውድነቱ እንዲረጋጋ ህገወጦችን ከማጋለጥ ጀምሮ በማንኛውም ጉዳይ ከአዲሱ መንግስት ጎን እንቆማለን ነው ያሉት፡፡

ነዋሪዎቹ ፤ ዛሬ በተካሄደው የአዲሱ መንግስት ምስረታ  ለተመረጡ ወኪሎች  መልካም የስራ ዘመን ተመኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም